በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አካባቢ የሚሰጠውን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አካባቢ የሚሰጠውን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል

ጂንካ፤ መስከረም 5/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አካባቢ የሚሰጠውን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ እንድሪያስ ጌታ(ዶ/ር ) እና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች በደቡብ ኦሞ ዞን በአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ የተከናወኑ ተግባራት ያመጡትን ውጤት ተመልክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የአርብቶ አደር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሚሊዮን ተክሌ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አካባቢ የሚሰጠውን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል።
የዚህ አካል የሆነውና በደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ ቡነከርሰሌ ቀበሌ የቡነከር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እና በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተመጻሕፍትና የአስተዳደር ቢሮዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ምዕራፍ ሀብታሙ፥ ትምህርት ቤቱ ስራ በጀመረበት ወቅት ለመማር ማስተማሩ እምብዛም አመቺ ባልሆኑ በጭቃ በተገነቡ መማሪያ ክፍሎች ሲካሄድ እንደነበር አንስተዋል።
አሁን የተገነቡት አነዚህ የመማሪያ ክፍሎች ቀደም ሲል የነበሩትን ጠባብ የመማሪያ ክፍሎችን በመቀየር የመማር ማስተማር ስራውን በማቀላጠፍ ለትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የራሳቸው ድርሻ እንደሚኖራቸው አክለዋል።
የትምህርት ቤቱ መገንባት የተማሪዎች ቁጥር እንዲጨምር በማገዙ በአዲሱ የትምህርት ዘመን 470 ተማሪዎች መቀበሉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስ የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር መጀመሩንም አንስተዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ እንድሪያስ ጌታ(ዶ/ር)፤በአርብቶ አደሩ አካባቢ የትምህርት ተሳትፎን ለማሳደግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ውጤት እያመጡ መሆናቸውን አንስተዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የተጀመረው ጥረት እንዲሳካም ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።