ቀጥታ፡

የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ጥናት በኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ያለው አበርክቶ የጎላ ነው

ሀዋሳ/ወላይታ ሶዶ/ ጂግጂጋ ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ)፦ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ጥናት ጠቃሚ የመረጃ ግብዓት በማስገኘት በኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ያለው አበርክቶ የጎላ መሆኑ ተመላከተ፡፡   

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሀዋሳ፣ የሶዶ እና የጂግጂጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የሀገር አቀፍ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ጥናት ለማካሄድ የመረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች ለ25 ቀናት የሚቆይ ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡


 

በሀዋሳ በተጀመረው ስልጠና ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሲዳማ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ  አራርሶ ገረመው (ዶ/ር) እንዳሉት የቆጠራ ጥናቱ ጠቃሚ የሆኑ የመረጃ ግብዓቶችን በማስገኘት በኢኮኖሚያዊ ልማት ሥራው ላይ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ የጎላ ነው፡፡


 

በተለይም ጥቅል ዓመታዊ ምርትን ለመገመትና መረጃን መሠረት ያደረገ የጠራ ዕቅድ እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል ሚና እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሀዋሳ ስታቲስቲክስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አሰጋሽ አሰፋ የቆጠራ ጥናቱ ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ በርካታ አላማዎችን በውስጡ የያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


 

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጠው ሥልጠና ሀዋሳን ጨምሮ ከሁሉም የሲዳማ ክልል ዞኖች እንዲሁም ከጌዴኦ፣ ከአማሮና ቡርጂ ዞኖች የተውጣጡ መረጃ ሰብሳቢዎች፣ ተቆጣጣሪዎች እና የስታቲስቲክስ ባለሙያዎች የተካተቱበት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ሀገራዊ የቆጠራ ጥናቱ  በሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥር በከተሞች በአንድ ሺህ 709 ቦታዎች እንዲሁም በገጠር በአንድ ሺህ 89 ቦታዎች ላይ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ በተጀመረው ስልጠና ላይም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕላን ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈቃደስላስ ቤዛ፤ ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ የሚተገበር የመካከለኛ ዘመን የስታቲስቲክስ ልማት ዕቅድ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎትና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ትብብር ሲተገበር ቆይቷል ብለዋል።


 

ስልጠናው ብቃት ያላቸውን መረጃ ሰብሳቢዎች፣ ተቆጣጣሪዎችንና ስታቲስቲክስ ባለሙያዎች በማፍራት ጥራት ያለውን መረጃ ለመሰብሰብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ዕቅዱም ከሀገራዊ የልማት አጀንዳዎች፣ ከዘላቂ ልማት ግቦች እና ከሌሎች አህጉራዊና ቀጠናዊ የልማት ዕቅዶች ጋር የሚናበብ መሆኑንም ተናግረዋል።

በማስጀመሪያው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው እንደ ዞን በቆጠራው የሚገኙ ውጤቶች ኢኮኖሚያዊ ዘርፎቻችንን ከመደገፍ በተጨማሪ ነገን ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚሰጠው ስልጠና 580 ሰልጣኞች መሳተፋቸውን የጠቆሙት በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሶዶ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም እስጢፋኖስ በበኩላቸው ሰልጣኞቹ 810 የቆጠራ ቦታዎችን እንደሚሸፍኑም ገልጸዋል።


 

በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጸዳሉ አየለ፤ ስልጠናው ለ9ዐዐ ሰልጣኞች እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አብዲ አህመድ (ዶ/ር)  ዩኒቨርሲቲው ስልጠናውን ለሁለተኛ ጊዜ እንዳዘጋጀ ጠቁመው ሰልጣኞች በዩኒቨርሲቲው የ25 ቀናት ቆይታ እንደሚኖራቸውም አስታውቀዋል። 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም