ቀጥታ፡

የትምህርት ሥርዓቱ ሪፎርም አንዱ የትኩረት አቅጣጫ የጊዜ አጠቃቀም ነው - ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ)፦ የትምህርት ሥርዓቱ ሪፎርም አንዱ የትኩረት አቅጣጫ  የጊዜ አጠቃቀም መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ የ2018 የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ቀደም ሲል ወጥ ያልነበረውን የትምህርት ማስጀመሪያና ማጠናቀቂያ ጊዜን ማስተካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የ2018 የትምህርት ዘመን ዛሬ በይፋ መጀመሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ተማሪዎች መማር ያለባቸውን የትምህርት ሰዓት በአግባቡ ሊማሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህን ለማድረግም ተማሪዎች ትምህርት ቤት ከተከፈተ ጀምሮ በትምህርት ገበታቸው ላይ ተገኝተው ትምህርት በመከታተል ዕውቀት መቅሰም እንዳለባቸው ነው የገለጹት።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ከ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት መዘግየት ጋር ተያይዞ ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬ ትምህርት አልጀመሩም።

ይሁንና ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ስራቸውን ይጀምራሉ ብለዋል።

ከትምህርት ሥርዓቱ ሪፎርም ጋር ተያይዞ ትምህርት ከተጀመረ በኋላ የሚባክን ጊዜ አይኖርም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን የጊዜ አጠቃቀማቸውን ማስተካከል እንዳለባቸው አንስተዋል።

ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ከትምህርት ሥርዓቱ የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም