ኮርፖሬሽኑ የ22 ሰብሎችን 90 ዝርያዎች የማባዛት ሥራ እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ የ22 ሰብሎችን 90 ዝርያዎች የማባዛት ሥራ እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከ20ሺህ ሔክታር በሚልቅ መሬት ላይ የ22 ሰብሎች 90 ዝርያዎችን እያባዛ መሆኑን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽንና ማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራ አመራር ሥራ አስኪያጅ ጋሻው አይችሉህም እንዳሉት፤ በ2016/2017 የምርት ዘመን በኮርፖሬሽኑ እርሻዎች፣ በሰፋፊ ኮንትራት አባዥ ማሳዎች እና በአርሶ አደር ማሳ 20ሺህ 627 ሔክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል።
ከዚህም 464ሺህ 270 ኩንታል ምርት ማምረት መቻሉን ለኢዜአ ተናግረዋል።
የምርት አፈጻጸሙ ካለፉት ሦስት ዓመታት ክንውኖች አማካይ አንጻር 34 በመቶ እንዲሁም ከ2015/16 የምርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር 10 በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ባሉት ስድስት የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ጣቢያዎች፣ በመንግሥትና የግል እርሻዎች እንዲሁም በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች ማሳ በኮንትራት እየሠራ ነው ብለዋል።
በዚህም ከ20ሺህ ሔክታር በሚልቅ መሬት ላይ የ22 ሰብሎችን 90 ዝርያዎች እያባዛ መሆኑን ነው የገለጹት።
በዓመትም በአማካይ ከ450ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ለተጠቃሚዎች እያቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህን ተከትሎ በሀገር ደረጃ ከሚቀርበው የምርጥ ዘር ፍላጎት 33 በመቶ ማሟላቱን አንስተዋል።
ኮርፖሬሽኑ ከምርጥ ዘር ማባዛት ጎን ለጎን ወደ ውጭ የሚላኩ ሰብሎች፣ የምግብ እህል፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሣት እርባታና የማር ምርት ላይ በስፋት ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።