ቀጥታ፡

የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በዘርፉ ለሚዘጋጁ እቅዶች፣ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ትክክለኛ ግብዓት ለማግኘት ያግዛል

ሐረማያ/ ሮቤ/ ድሬዳዋ ፤ መስከረም 5/2018(ኢዜአ)፦የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ  በዘርፉ ለሚዘጋጁ እቅዶች፣ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ትክክለኛ ግብዓት  ለማግኘት እገዛ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ገለጸ።

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ላይ ለሚሰማሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው።


 

የሐረር ስታቲስቲክስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከሐረሪ ክልል፣ ከምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ማያ ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡና የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ላይ ለሚሰማሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተጀመረው በዚሁ ስልጠና ላይ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሐረር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሙክታር ጀማል እንደገለጹት የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራው በከተሞች ሙሉ በሙሉ እንደሚከናወን ገልጸው፤ በገጠር ደግሞ በናሙና በተለዩ ቦታዎች ላይ የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሆኑም በቅርንጫፉ ሥር በአጠቃላይ  በ1ሺህ 143 ቦታዎች ላይ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ እንደሚካሄድ ገልጸው በዛሬው እለትም በአካባቢው በሚከናወነው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ለሚሳተፉ 661 መረጃ ሰብሳቢ፣ ተቆጣጣሪዎችና ሌሎች ባለሙያዎች ለ25 ቀናት የሚቆይ ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።

ስልጠናውም መረጃ ሰብሳቢዎች  ጥራትና ወቅቱን የጠበቀ ፣ ተገቢነትና ተአማኒነት ያለውን መረጃ እንዲሰበስቡ የሚያስችል  ክህሎት እንዲያገኙ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የባሌ ዞንን ጨምሮ ከሌሎች አምስት ዞኖች ለተመለመሉ ባለሙያዎች ለ25 ቀናት የሚቆየውን በተግባር የተደገፈ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በሮቤ ከተማ እየሰጠ ነው። 

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የባሌ ሮቤ ክላስተር ሥልጠና አስተባባሪ አቶ ቡሎ ፈዬራ እንዳሉት አገልግሎቱ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን መልምሎ ካሰለጠነ በኋላ ወደ መስክ በማሰማራት ተጨባጭ ሥራዎች እንዲያከናውኑ ለማድረግ እየሰራ ነው። 


 

ከባሌ ዞን፣ምሥራቅ ባሌ፣ምዕራብ ቦረና፣ ምዕራብ አርሲ እና ከሶማሌ ክልል ሊባን ዞኖች ለተውጣጡ ከ800 ለሚልቁ ባለሙያዎች እየተሰጠ የሚገኘው በተግባር የተደገፈ ሥልጠና የዚሁ  አካል መሆኑን አመልክተዋል። 

ከቆጠራው የሚገኙ መረጃዎች በዘርፉ ለሚዘጋጁ እቅዶች፣ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ትክክለኛ ግብዓት በመሆን እገዛ ያደርጋል ያሉት ደግሞ የስልጠናው አስተባባሪ  አቶ እንዳሻው ፈለቀ ናቸው።


 

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የባሌ ጎባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽመልስ አሰፋ በበኩላቸው፣ የባለሙያዎች የግንዛቤ ሥልጠና በኢኮኖሚ ቆጠራው መርሐግብር የጠራ መረጃ በማሰባሰብ ለሚፈለገው አገራዊ ዓላማ እንዲውል እገዛ እንዲያደርጉ ያግዛል። 


 

በተመሳሳይ ስልጠናው የድሬዳዋ አስተዳዳርና የሶማሌ ክልል ሲቲ ዞንን በማካተት በድሬደዋ መሰጠት ተጀምሯል።

ዛሬ በተጀመረውና ለ25 ተከታታይ ቀናት በሚዘልቀው ስልጠና ላይ የተሳተፉት የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ግርማና የድሬደዋ አስተዳደር ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽነር ኃይለማርያም ዳዲ ቆጠራውን አስመልክተው ገለፃ ሰጥተዋል።


 

አቶ ሙሉጌታ ግርማ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ቆጠራው የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድንና የኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ጉዞን ለመገምገምና የፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦችን ለማመንጨት መሠረታዊ ሚና እንደሚያበረክት  አስታውቀዋል።

በቆጠራው በገጠር በናሙና በከተሞች ደግሞ በሁሉም የኢኮኖሚ ድርጅቶች ላይ ተገቢው መረጃ በጥራትና በላቀ ጥንቃቄ ይካሄዳል ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽነር ኃይለማርያም ዳዲ በበኩላቸው ቆጠራው ለአገራችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድገት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።


 

የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በኢኮኖሚው ዘርፍ  የተመዘገበውን ስኬት ለማስቀጠልና በዘርፉ ለሚዘጋጁ እቅዶች ግብዓት በመሆን እንዲሁም ለጥናትና ምርምር ስራዎች  እገዛ እንደሚያደርግ ታውቋል።

በኢኮኖሚ ቆጠራው በጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች፣ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች፣ የገንዘብና ኢንሹራንስ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች የግልና የመንግሥት የኢኮኖሚ ድርጅቶችና ባለሀብቶች እንደሚጠኑም እንዲሁ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም