ኮሚሽኑ ዘመናዊና ቀልጣፋ የጉምሩክ አገልግሎትን የሚያጠናክር ተቋማዊ አቅም እየገነባ ነው - ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ዘመናዊና ቀልጣፋ የጉምሩክ አገልግሎትን የሚያጠናክር ተቋማዊ አቅም እየገነባ ነው - ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት በመስጠት በሀገራዊ ዕድገት ላይ ጉልህ አሻራ ማሳረፍ የሚያስችል ተቋማዊ አቅም እየገነባ መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ገለጹ።
የጉምሩክ ኮሚሽን የአዳዲስ የጉምሩክ ሠራተኞች የምረቃ ስነ-ስርዓት እያካሄደ ይገኛል።
በመርኃ ግብሩ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ፣ የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በወቅቱ፤ ኮሚሽኑ ከለውጡ ወዲህ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ለማዘመን በርካታ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
በዚሁ መሰረት አዲስ በተሻሻለው የኮሚሽኑ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሰረት ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተመልምለው ስልጠና እና የብቃት ፈተና ወስደው ያለፉ ከ3ሺህ 200 በላይ አዲስ የጉምሩክ ባለሙያዎችን አስመርቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ማዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።
እነዚህ አዲስ ሠራተኞች ከዛሬ ጀምሮ የጉምሩክ አሰራርን በማዘመንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ልማት ላይ ጉልህ አሻራቸውን እንደሚያሳርፉ ተናግረዋል።
የጉምሩክ አገልግሎት ውጤታማነት ሀገራዊ ገቢንና ኢንቨስትመንትን እንደሚያሳድግና የንግድ ሥርዓቱን እንደሚያሳልጥ በማንሳት፤ ለስኬታማነቱ ተቋማዊ ኃላፊነታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ለዚህም ዛሬ ተመርቀው ሥራ የሚጀምሩት አዲስ ሠራተኞች በታማኝነት፣ በትህትና እና በትጋት ሀገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።