የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ለሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች መነሳሳትን የፈጠረ አኩሪ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ለሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች መነሳሳትን የፈጠረ አኩሪ ተግባር ነው
ሮቤ/ ቢፍቱ ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ለሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች መነሳሳትን የፈጠረ አኩሪ ተግባር መሆኑ ተገለጸ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ አመራሮች የእግር ኳስ ጨዋታ አካሄደዋል።
በሮቤ ከተማ በተካሄደው የእግር ኳስ ጨዋታ የተሳተፉት የባሌ ዞን እግር ኳስ ቡድን ተወካይ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ሀይሌ ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አኩርቶናል ብለዋል።
ይህ ስኬት የበሳል አመራር ጥበብና የሕዝብ ቅንጅታዊ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ስኬትን በማስመልከት አመራሩና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የድጋፍ ሰልፍ፣ የጎዳና ላይ ሩጫና በእግር ኳስ ጨዋታ በየደረጃው መቀጠሉን አንስተዋል።
የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ አለማየሁ ቱሉ በበኩላቸው፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ለመድገም መነሳሳትን የፈጠረ አኩሪ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማው ነዋሪ የግድቡን መጠናቀቅ በማስመልከት የተሰማውን ደስታ በተለያየ መልኩ መግለጹን አንስተዋል።
ሌላው የጨዋታው ተሳታፊ አመራር አቶ ታጁዲን ሀሱ፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበት የአብሮነትና የአንድነት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ስኬቱን በሌሎችም ልማቶች ላይ ለመድገም የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ውስጥ በተለያየ መልኩ የበኩላቸውን ማበረከታቸውን ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መተባበር ለስኬት እንደሚያበቃ ያየንበት ነው ያሉት ደግሞ አቶ ኤሊያስ ሁሴን ናቸው።
በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን የቢፍቱ ከተማና ጉራፈርዳ ወረዳ ነዋሪዎች በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬት ደስታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል።
"በሕብረት ችለናል" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ሰልፍ ከተሳተፉት መካከል አቶ ሞላ ካሳሁን በሰጡት አስተያየት፤ የዓባይ ወንዝ ሀገሩን ሊያለማ በሀገሩ ልጆች የተደመረ አቅም በመመለሱ ተደስተናል ብለዋል።
ነገም ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በትብብር በመገንባት የኢትዮጵያን ከፍታ ለማየት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
አቶ አለማየሁ ቡርጅ በበኩላቸው፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለትውልድ የሚተላለፍ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክታችን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት እጅ ለእጅ ተያይዘን በስኬታማነት መጓዛችንን ቀጥለናል ያሉት ደግሞ የቢፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኦሚስ ካሲካራ ናቸው።