ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የቻይና ሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ዋንግ ዢያሆንግ በፀጥታ እና በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ዙሪያ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የቻይና ሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ዋንግ ዢያሆንግ በፀጥታ እና በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ዙሪያ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/ 2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል የፀጥታ እና የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክቶች ደኅንነት እንዲጠናከር እንዲሁም የወንጀል መከላከል አቅምን የበለጠ ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በቻይና በሚካሄደው የ2025 ዓለም አቀፍ የህዝብ ደህንነት ትብብር ፎረም ላይ ለመካፈል ወደ ቻይና ባቀኑበት ወቅት በቤጂንግ ከተማ ከቻይና የምክር ቤት አባልና የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ዋንግ ዢያሆንግ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ተቋማት በፀጥታ እና በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከም ተስማምተዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የቻይና መንግሥት እያደረገ ላለው ድጋፍና እገዛ ምስጋና አቅርበው በኢትዮጵያ ለሚገኙ የቻይና ዜጎች፣ ተቋማት እና ፕሮጀክቶች የሚደረገው የደኅንነት ጥበቃ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የቻይና የምክር ቤት አባልና የሕዝብ ደህንነት ሚኒስትር ዋንግ ዢያሆንግ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የደረሱበትን ስምምነት መሠረት ሁለቱ ተቋማት የፀጥታ እና የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክቶች ደኅንነት እንዲጠናከር እንዲሁም የወንጀል መከላከል አቅምን የበለጠ ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በውይይቱ ወቅት አንስተዋል።
የዓለም አቀፍ የሕዝብ ደህንነት ትብብር ፎረም በነገው ዕለት እ.ኤ.አ መስከረም 16 ቀን 2025 በቻይና የሚካሄድ ሲሆን፤ ከ176 ሀገራት እና ክልሎች የተውጣጡ ከ800 በላይ ተሳታፊዎች እንዲሁም 14 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁማል።