በትውልዱ የጋራ ርብርብ ለስኬት የበቃው የህዳሴ ግድብ በክልሉ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሯል -አቶ አወሉ አብዲ - ኢዜአ አማርኛ
በትውልዱ የጋራ ርብርብ ለስኬት የበቃው የህዳሴ ግድብ በክልሉ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሯል -አቶ አወሉ አብዲ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5 /2018(ኢዜአ)፦ በትውልዱ የጋራ ርብርብ ለስኬት የበቃው የህዳሴ ግድብ በኦሮሚያ ክልል ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት ፈጥሯል ሲሉ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መጠናቀቅን ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ ስፖርትና ወጣቶች ቢሮ አስተባባሪነት የክልሉ አመራሮችና ሰራተኞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርገዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ፤ የአሁኑ ትውልድ በጋራ ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ የህዳሴን ግድብ በማሳካት አንጸባራቂ ውጤት ለአለም ማሳየት ችሏል።
ይህም በክልሉ ህዝብ ዘንድም ሆነ በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት መፍጠሩን ገልጸው፤ በዚሁ መነሳሳትም ክልሉ ቀጣይነት ያለውን ሰላም በማጽናት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ህዝቡ በህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ያሳየውን ትብብር በሌሎች የልማት ስራዎች ላይም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ አወሉ አንስተዋል።
አያይዘውም በክልሉ የተለያዩ የልማት ኢንሼቲቮችን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑም አንስተዋል።
እንዲሁም የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በአንድ ማዕከል በማድረግ ህዝቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በስፖርታዊ እንቅስቃሴው ላይ ከተሳተፉት መካከል በክልሉ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ቆንጂት በቀለ እንዳሉት የክልሉ ህዝብ ከግድቡ ፕሮጀክት ጅማሮ አንስቶ በገንዘብና በዓይነት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
ለዘርፈ ብዙ ድጋፉ ህዝቡን ያመሰገኑት ወይዘሮ ቆንጂት በቀለ ድጋፉን በሌሎች የልማት ስራዎች ላይም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።