የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በመተባበር ከድህነት መውጣት እንደሚቻል ያሳያል - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በመተባበር ከድህነት መውጣት እንደሚቻል ያሳያል
ሆሳዕና ፤ መስከረም 5 /2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በመተባበር ከድህነት መውጣት እንደምንችል ማሳያ ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ረዳት ተጠሪ አቶ ይግለጡ አብዛ ገለፁ፡፡
"በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን በማስመልከት የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል፡፡
የክልሉ መንግሥት ረዳት ተጠሪ አቶ ይግለጡ አብዛ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በመተባበር ከድህነት መውጣት እንደምንችል ማሳያ ነው ብለዋል ፡፡
ህዝብንና ሀብትን በማቀናጀት ድህነትን ታሪክ ማድረግ እንደሚቻል የህዳሴው ግድብ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጥረት እውን ለማድረግ አጋዥ ነው ብለዋል።
በህዳሴው ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ ህዝቡ ያሳየውን ተነሳሽነት በማጠናከርም ለሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በማዋል የበለጸገች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ አሼቦ በበኩላቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በተባበረ ክንድ ለስኬት መብቃት እንደሚቻል ያሳየ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የክልሉ ህዝብ የራሱን አስተዋጽኦ ሲያበረክት ስለመቆየቱም አስታውሰዋል፡፡
የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን በትብብር ከተጓዝን በውስጣዊም ሆነ በውጫዊ ተግዳሮቶች ሳንበገር ሀገራችንን በራስ አቅም ማበልፀግ እንደምንችል ተምሳሌት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በትብብር በራስ አቅም ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ያለንን አቅም በተግባር ያሳየንበት ፕሮጀክት ነው ያሉት ደግሞ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ አቶ አበራ ሄቢሶ ናቸው ፡፡
የግንባታውን ሂደት ለማስተጓጎል የተደረጉ ጥረቶችን ለመመከት የተደረጉ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን አጠናክረን በማስቀጠል የተሻለች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ ይበልጥ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ በክልሉ የሆሳዕና ክላስተር፣ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ፣ የሀድያ ዞን፣ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደርና የሌሞ ወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡