ቀጥታ፡

የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ወሳኔ አሳለፈ

ሐረር፤ መስከረም 5 /2018(ኢዜአ)፦ የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ባካሄደው ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ በመጀመሪያ የተወያየው በተሻሻለው የመንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን፤ የአዋጁ መሻሻል የመንግስት ተቋማት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃትና በውጤታማነት እንዲወጡ የሚያስችልና ብዝሃነትና አካታችነትን ያገናዘበ ኢትዮጵያን የሚመስል የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓት መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ ነው።

ረቂቅ አዋጁ የመንግስት አስተዳደር አገልግሎትን ፍትሃዊ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ እና የተገልጋዮችን ፍላጎትና ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ከመሆኑም በተጨማሪ የሰራተኞች ምልመላና መረጣም በውድድር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን፤ በሰራተኞች መካከል ጤናማ ውድድርን ለማሳደግና ምርታማነትን ለማጎልበት፤ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሚያግዝ ስለሆነ ረቂቅ አዋጁ ለክልሉ ካቢኔ ቀርቧል።

ካቢኔውም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ይፀድቅ ዘንድ ወደ ክልሉ ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ መወሰኑም ተገልጿል።


 

መስተዳድር ምክር ቤቱ (ካቢኔው) ቀጥሎ የተወያየው የወንዞችና የተፋሰስ ዳርቻዎችን ከብክለት ለመከላከል፣ የቁጥጥር ሥርዓት የወጣ ረቂቅ ደንብ ነው።

ረቂቅ ደንቡ በክልሉ በወንዞች ላይ ሲደርስ የቆየውን የአካባቢ ብክለትና ጉዳት በማስቀረትና በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። በተለይም በአሁኑ ወቅት በክልሉ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ሥራዎች በወንዞችና የተፋሰስ አካባቢዎች ላይም እንዲጠናከር በማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያበረክታል።

ረቂቅ ደንቡም ሀገራዊና ክልላዊ የሕግ ማዕቀፎችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን የክልሉ ማኅበረሰብ በጤናማ፣ ጽዱና ውብ በሆነ አካባቢ እንዲኖር የሚያስችል አሠራርን ለመዘርጋት የሚያግዝ በመሆኑ ረቂቅ ደንቡ ለክልሉ መስተዳድር ምክር ቤቱ መቅረቡ ተጠቅሷል።

መስተዳድር ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምፅ በማፅደቅ ከዛሬ መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውል መወሰኑ ተገልጿል።

በሶስተኛነት መስተዳድር ምክር ቤቱ የተወያየው የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓትን ለመደንገግ በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን ረቂቅ አዋጁም የአስፈጻሚ አካላትን የአገልግሎት አሰጣጥን እንዲያዘምኑና ተገልጋዮች በተገቢው መንገድ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

መስተዳድር ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በጥልቀት ተወያይቶ ይፀድቅ ዘንድ ወደ ክልል ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል ተብሏል።

ቀጥሎም መስተዳድር ምክር ቤቱ በጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ መክሯል።

ረቂቅ አዋጁ በክልሉ የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደርን በተመለከተ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 114/2005 በተለይም የዲሲፕሊን ጉባኤ ያለመቋቋም፤ የዲሲፕሊን ጥፋትና ቅጣት ድንጋጌ ውስንነት፣ ክልላዊ የጠበቆች ማህበር በህግ ማዕቀፍ ላይ አለመካተቱ፣ የጥብቅና ፍቃድ አሰጣጥና መስፈርቶች ላይ ያሉ ክፍተቶች፣ የጥብቅና የሙያ ግዴታዎች በዝርዝር ያለመደንገግ እንዲሁም ከጠበቆች አስተዳደር ቦርድ ጋር በተያያዘና ሌሎች ውስንነቶች በመኖሩ የአዋጁን ማሻሻያ አስፈላጊ እንዳደረገው ተመላክቷል።

አዋጁ መሻሻሉ በክልሉ የጥብቅና አገልግሎትና አስተዳደር የታለመለትን ዓላማ ማሳካትና የጠበቆች አስተዳደር ጋር በተገናኘ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ለዜጎች የፍትህ ዘርፍ ተደራሽነትን ለማሳደግ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ካቢኔው በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ተወያይቶ ተጨማሪ ግብዓት በማከል ይፀድቅ ዘንድ ወደ ክልል ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም መስተዳድር ምክር ቤቱ በሌሎች አጀንዳዎች ላይም ውይይት በማድረግ ውሳኔ ማሳለፉም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም