ዘመናዊ የመንግሥት አገልግሎት የሚፈልገውን ዕውቀትና ክህሎት የታጠቀ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጓል-ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊ የመንግሥት አገልግሎት የሚፈልገውን ዕውቀትና ክህሎት የታጠቀ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጓል-ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት የሚፈልገውን ዕውቀትና ክህሎት የታጠቀ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ የጀመራቸውን ተግባራት የሚያጠናክር አደረጃጀት እንዲኖረው በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲን እንደ አዲስ ለማደራጀት በትምህርት ሚኒስቴር፣ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች የተካሄደ የጥናት ውጤት ይፋ ሆኗል።
የጥናቱ ውጤት ዩኒቨርሲቲው ለኢትዮጵያ የመንግሥት አገልግሎት ዕድገት ተጨማሪ አቅም በሚሆን አግባብ መደራጀት እንዳለበት አመላክቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ባላቸው ጸጋና ልምድ ላይ ትኩረት አድርገው ማስተማር ይገባቸዋል።
ይሁንና ቀደም ሲል ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ የትምህርት አይነቶችን እንደሚሰጡ በማንሳት፥ ይህም ሀገሪቱ በምትፈልጋቸው ዘርፎች ላይ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ክፍተት ፈጥሯል ብለዋል።
ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት ዩኒቨርሲቲዎች በልዩነት የሚያስተምሩባቸው የትምህርት አይነቶች ሊኖሩ እንደሚገባ ተወስኖ ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት እንዲችል ጥናት ላይ የተመሰረተ የማሻሻያ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህ መሰረት ለመንግስት የልማት ሥራዎች ተደማሪ አቅም የሚፈጥር የሲቪል ሰርቪስ መሪዎችና ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ መድረስ የምትፈልገው የዕድገትና የስልጣኔ ደረጃ ላይ መድረስ የሚያስችል ጠንካራ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ባለሙያዎችን ማፍራት የሚያስችል አደረጃጀትና አሰራር ሊከተል እንደሚገባ በጥናቱ መመላከቱን አንስተዋል።
የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሸነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው የአመራርና ባለሙያዎችን አቅም በሚፈለገው መልኩ መገንባት የሚያስችለውን ቁመና እንዲይዝ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደርን ማዘመን የሚያስችል ሁለንተናዊ አቅም እንዲኖረው እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) ዩኒቨርስቲው የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሪዎችና ባለሙያዎችን ማብቃት በሚያስችል ቁመና እንዲደራጅ መንግስት ውሳኔ ማሳለፉን አስታውሰዋል።
በዚህ መሰረት ሲቪል ሰርቪሱን የሚያዘምን መሪና ባለሙያ ማፍራት የሚያስችለውን የተለየ የትምህርት አሰጣጥ ይከተላል ብለዋል።