የኃይሌ ገብረስላሴ እና የፖል ቴልጋርት የአቴንስ ትንቅንቅ ሲታወስ - ኢዜአ አማርኛ
የኃይሌ ገብረስላሴ እና የፖል ቴልጋርት የአቴንስ ትንቅንቅ ሲታወስ

እ.አ.አ 1997 ስድስተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በግሪክ አቴንስ የተካሄደበት ወቅት ነበር። ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በሁለቱም ጾታዎች ተሳትፎ አድርጋለች።
5000 ሜትር፣ 3000 ሜትር መሰናክል፣ 10000 ሜትር እና ማራቶን በወንዶች እንዲሁም 1ሺህ 500፣ 5000 ሜትር፣ 10000 ሜትር እና ማራቶን ኢትዮጵያ በሴቶች የተሳተፈችባቸው ርቀቶች ነበሩ።
የ10000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ ድንቅ የሚባል ፉክክር ከታየባቸው ውድድሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።
ውድድሩ የዓለም ኮከቡንና የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑን ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እና የኬንያውን የምንግዜም ተቀናቃኙን ፖል ቴርጋት ያገናኘ ነበር።
ሁለቱ አትሌቶች በፍጻሜው ላይ የተገናኙት የብቃት ጫፍ ላይ በነበሩበት ወቅት ላይ ነው።
የአቴንሱ ውድድር የአትሌቶቹ በወቅቱ እያደገ የመጣ ተቀናቃኝነት ላይ አዲስ የታሪክ ምዕራፍን የከፈተ እና ፉክክራቸው እ.አ.አ በ199ዎቹ የረጅም ርቀት ውድድሮች በያኝ ነበር ማለት ይቻላል።
የ10000 ሜትር ፍጻሜው ሁሉም የአትሌቲክስ አፍቃሪ የገመተውን እልህ አስጨራሽ ፉክክር የተመለከተበት ነበር።
ቴርጋት በውድድሩ ኃይሌን የ10000 ሜትር የበላይነት ለማስቆም የሮጠበት በአንጻሩ ኢትዮጵያዊው ኮከብ አትሌት ትዕግስት በተሞላበት፣ ከተቀናቃኙ ቅርብ ሆኖ ትንፋሹን በመለካትና ጉልበቱን በመጠበቅ ሮጧል።
በመጨረሻዎቹ ዙሮች ውጥረቱ እያጋለ የመጣ ሲሆን ሁለቱ ታላላቅ አትሌቶች ከሌሌቹ አትሌቶች ተነጥለው በመውጣት ፉክክራቸውን ቀጠሉ።
ቴርጋት ለማሸነፍ ቀድሞ ቢወጣም በድንቅ የአጨራረስ ብቃት የሚታወቀው ኃይሌ በመጨረሻው ዙር የአጸፋ ምላሹን ሰጠ።
ኃይሌ የአንገት ለአንገት ትንቅንቁን በብቃት በመወጣት የአሸናፊነቱን መስመር ተሻግሮ የወርቅ ሜዳሊያ አጠለቀ።
27 ደቂቃ ከ24 ሴኮንድ ከ58 ማይክሮ ሴኮንድ አትሌቱ ያሸነፈበት ጊዜ ነው።
ቴርጋት በ27 ደቂቃ ከ28 ሴኮንድ ከ56 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀቀ።
የሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ወርቅ ኢትዮጵያ በአቴንሱ ሻምፒዮና ያገኘችው ብቸኛ ሜዳሊያ ነበር።
የአቴንሱ ፍልሚያ የኃይሌን የበላይነት ዳግም ያሳየ ሲሆን ቴርጋት ቢሸነፍም እልህ አስጨራሽ ፉክክር አድርጓል።
ሁለቱ ድንቅ አትሌቶች እ.አ.አ በ2020 በሲድኒ በተካሄደው 27ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ 10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ በድጋሚ ተገናኝተው ዓለምን ቁጭ ብድግ ያሰኘ ፉክክር አድርገዋል።
ኃይሌ አሁንም በሽርፍራፊ ሴኮንዶች ተቀናቃኙን አስከትሎ በመግባት አሸንፏል።
የ1997ቱ የአቴንስ የዓለም ሻምፒዮና የ10000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ የሁለቱን የምንግዜም ድንቅ የረጅም ርቀት ሯጮች ብርቱ ፉክክር አንጥሮ ውድድር ሆኖ ሁሌም ሲወሳ ይኖራል።