ቀጥታ፡

ትውልዱ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ያሳየውን ትብብር በሌሎች ዘርፎችም በማጠናከር ድህነትን ማሸነፍ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ መስከረም 5/2018(ኢዜአ)፦ ትውልዱ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ያሳየውን ትብብርና አንድነት በሌሎች ዘርፎችም በማጠናከር ድህነትን ማሸነፍ ላይ መረባረብ እንደሚገባው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኦሞድ ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን አስመልከቶ በጋምቤላ ክልል ደረጃ የደስታና ድጋፍ ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂደል።


 

ርዕሰ መስተዳድሯ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ጀግኖች አባቶች ሀገራቸውን ከውጪ ወራሪ ጠብቀው በማቆየት ያሳዩትን አርበኝነት የዚህ ዘመን ትውልድም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደግሞታል ብለዋል።

ትውልዱ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድቡ ያሳየውን የልማት አርብኝነት በማጠናከር ድህነትን ለማሸነፍ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።


 

ኢትዮጵያ ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋዎች ያሏት ቢሆንም በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች ሀብቱ በተፈለገው ልክ ለምቶ ለህዝቡ ጥቅም ያለመዋሉን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የዘመኑ ትውልድ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ገንብቶ በማጠናቀቅ የልማት አርበኝነቱን በተግባር በማሳየት የማንሰራረት ጅማሮውን አብስሯል ብለዋል።

በተለይም ኢትዮጵያውያን ተባብረው ከሰሩ የማያሳኩት ልማትና የማይሻገሩት ፈተና እንደማይኖር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓይነተኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የታየውን የልማት ትብብርና መነሳሳት በሌሎች ልማቶች በመድገም የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን እድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ ተግቶ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ህዝብ ግድቡ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ላሳየው የነቃ ተሳትፎ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።


 

የክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ጋትቤል ቦል በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ጽህፈት ቤቱ ለሕዳሴ ግድቡ እውን መሆን መላውን የክልሉን ህዝብ በማስተባበር ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም የክልሉ ህዝብ በቦንድ ግዥ፣ በገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ በግድቡ ግንባታ ላይ ታሪካዊ አሻራቸውን በማስቀመጥ የዜግነት ኃላፊቱን ተወጥተዋል ብለዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ለዘመናት ስንናፍቀው የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን ሆኖ በማየታችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ሲሉ ገልጸዋል።

በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የህዳሴ ግድቡን የሚዘክሩ የተለያዩ መልዕክቶች፣ ባህላዊ ጭፈራዎችና ወታደራዊ ትሪኢቶች ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም