ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የልማት አቅሞችን ለኢኮኖሚያዊ እድገት ለማዋል የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው(ዶ/ር)

ሆሳዕና፤ መስከረም 5/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የልማት አቅሞችን ለኢኮኖሚያዊ እድገት ለማዋል የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በግብርና፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤቶችን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም በክልሉ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የተተገበሩ የተቀናጁ የልማት እቅዶች የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ክልሉ ያለውን የልማት አቅሞች ወደ ውጤት በመቀየር ሀገራዊ የማንሰራራት ጉዞን ለማገዝ ለግብርናው፣ ለማምረቻው፣

ለቱሪዝም፣ ለማዕድን እና ለዲጂታል ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀምና ዘመናዊ የአመራረት ዘዴን በመከተል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ አማራጮችን በመተግበር ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የግብዓትና ምርጥ ዘር ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ መሰራቱን ጠቁመዋል።

ይህም ዝናብ ብቻ ጠብቆ ከማረስ ተላቀው የውሃ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖና በሌሎችም ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል።

በዚህም በክልሉ ምርታማነትን በመጨመር አምራቹን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለገበያ ማረጋጋት የራሱን አበርክቶ ማድረጉን አክለዋል።

የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማጠናከርም የድጋፍና ክትትል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም የወጪና የገቢ ምርቶች በአይነትና በጥራት እንዲያድጉና ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ ምቹ መደላድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡

የክልሉን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በመጠበቅ የገቢ ማስገኛ እንዲሆኑ በጥናት የተደገፈ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጨምር በማድረጉ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም