ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች ፍጻሜ ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች ፍጻሜ ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2018(ኢዜአ)፦ በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ የ3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ከ55 በሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር ለሜቻ ግርማ፣ ጌትነት ዋለ እና ሳሙኤል ፍሬው ይሳተፋሉ።
አትሌት ለሜቻ እ.አ.አ በ2023 በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ እ.አ.አ በ2022 በአሜሪካ ኢውጂን በተደረገው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በኳታር ዶሃ በተከናወው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርቀቱ በተመሳሳይ የብር ሜዳሊያዎችን አግኝቷል።
ለሜቻ እ.አ.አ በ2023 በፓሪስ በተደረገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 7 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት መሆኑ ይታወሳል።
አትሌቱ በሻምፒዮናው ተሳትፎ ታሪክ የመጀመሪያውን ወርቅ ለማግኘት ከወቅቱ አሸናፊ ሞሮኳዊው ሶፊያን ኤል-ባካሊ ጋር የሚያደርገው ፉክክር ተጠባቂ ነው።
በውድድሩ ላይ የሚሳተፉት ጌትነት ዋለ 8 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ15 ማይክሮ ሴኮንድ እና ሳሙኤል ፍሬው 8 ደቂቃ ከ4 ሴኮንድ ከ34 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓታቸው ነው።
በቶኪዮ እየተካሄደ ባለው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ እስከ አሁን ሁለት የብር እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።