ቀጥታ፡

በግብርና ምርት ውል ትስስር አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው - ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2017(ኢዜአ)፡- ባለፉት ሦስት ዓመታት በግብርና ምርት ውል ትስስር በተለያዩ ዘርፎች ከዕቅድ በላይ መፈጸም መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የግብርና ምርት ውል ዴስክ ኃላፊ ሱልጣን መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በግብርና ምርት ውል ትስስር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ አፈጻጸማቸው እያደገ መጥቷል።

በዚህም መሠረት ከ2015 እስከ 2017 ዓ.ም በግብርና ምርት ውል ትስስር የሚፈጥሩ አስመራቾችን 1ሺህ 268 ለማድረስ ታቅዶ፤ 3ሺህ 490 ማድረስ መቻሉን ነው የተናገሩት።

እንዲሁም በግብርና ምርት ውል ትስስር የሚፈጥሩ አምራቾችን ቁጥር በሦስት ዓመት 9ሺህ 74 ለማድረስ ታቅዶ 18ሺህ 85 ማድረስ መቻሉን አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል 17ሺህ 79 ነጥብ 59 ሔክታር መሬት በግብርና ምርት ውል ትስስር ለመሸፈን ታቅዶ፤ 36ሺህ 74 ነጥብ 92 ሔክታር መሬት መሸፈኑን ተናግረዋል።

በግብርና ምርት ውል ትስስር የወጪ ምርት መጠንን ባለፉት ሦስት ዓመታት 21 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ 37 ነጥብ 78 ሚሊየን ኩንታል መላክ መቻሉን አንስተዋል።


 

በግብርና ምርት ውል ከአግሮ ኢንዱስትሪ(አስመራች) ጋር የተፈጠረ ትስስርን ሲያስረዱም፤ በአንድ አስመራች 7ሺህ ሔክታር በጉሎ ሰብል በመሸፈን በ1ሺህ አምራቾች 14ሺህ ቶን ተመርቷል ብለዋል።

በካሳቫ ምርት በተሰማሩ ሁለት አስመራቾች 4 መቶ ሺህ ሄክታር መሸፈኑን ጠቅሰው፤ 350 አምራቾች መኖራቸውንና 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን መመረቱንም ጠቁመዋል።

እንዲሁም 2ሺህ ሔክታር መሬት በቅመማቅመም ተሸፍኖ በሁለት አስመራቾች በ5ሺህ አምራቾች 2ሺህ 600 ቶን መመረቱን ጠቅሰዋል።

በቅባት እህልም 6ሺህ ሔክታር ተሸፍኖ በሦስት አስመራቾችና 200 አምራቾች 18ሺህ ቶን መመረቱን ነው የገለጹት።

በአቮካዶ ዘርፍም እንዲሁ በአራት አስመራቾች በ62 ኅብረት ሥራ ማኅበራት 848 ቶን መመረቱን ነው ጨምረው የተናገሩት።

በምርጥ ዘር ብዜትም በ6 አስመራቾች 715 ሔክታር መሬት በመሸፈን በ654 አምራቾች 2ሺህ 920 ቶን ማምረት ተችሏል ነው ያሉት።

በፍየል፣ በግ እና የዳልጋ ከብት ዘርፍ ሦስት አስመራቾችና 300 አምራቾች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በአጠቃላይ 20ሺህ እንስሳትን ማርባት መቻሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም