ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅ የአይቀሬው ብልጽግናችን ማረጋገጫ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅ የአይቀሬው ብልጽግናችን ማረጋገጫ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅ የኢትዮጵያ የመቻል ማሳያ ብሎም የአይቀሬው ብልጽግናችን ማረጋገጫ ብሔራዊ ምልክት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትና ድል አድራጊነት በነቂስ ወደ አደባባይ በመትመም ደስታውን ለገለፀው ብሔራዊ ጀግኖቹን ላመሰገነው የአዲስ አበባ ነዋሪ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
በርካቶች ከመቀነታቸው ፈትተው፣ካላቸው ቀንሰው፣ ሕጻናት ጭምር ያላቸውን ለቦንድ መግዣ በማዋል በብርቱዎች ተገንብቶ ለፍፃሜ የበቃውን የሕዳሴ ግድብ ድል የከተማችን ነዋሪ በድምቀት አክብሯል ሲሉም ገልጸዋል።
የከተማችን ነዋሪዎች የሌሊት ቁርና ዝናብ ሳይበግራችሁ፤የዘመናት፣ የትውልዶች ትግል ውጤት የሆነው ድላችሁን በጋራ አክብራቹሃል ያሉት ከንቲባዋ፤ ለዚህ ድል ከነበራችሁ ደጀንነት አንፃር ይገባቹሀል ብለዋል።
ይህ ድል የኢትዮጵያ የመቻል ማሳያ፤ የአይቀሬው ብልጽግናችን ማረጋገጫ ብሔራዊ ምልክት ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።