በትምህርት ዘርፉ እየተደረገ ያለው ሪፎርም በ2017 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት እንዲሻሻል አስችሏል-የትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ዘርፉ እየተደረገ ያለው ሪፎርም በ2017 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት እንዲሻሻል አስችሏል-የትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፦የትምህርት ስርዓቱን ስብራት ለመጠገን በዘርፉ እየተደረገ ያለው ሪፎርም በ2017 የትምህርት ዘመን የ12 ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ውጤት ካለፉት ዓመታት የተሻለ እንዲሆን ማስቻሉን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
እስከ ነገ ቀን 6 ሰዓት ድረስ የተማሪዎች ውጤት እንደሚለቀቅም ተገልጿል።
በ2017 የትምህርት ዘመን የተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትን በተመለከተ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት በ2017 ፈተና ከወሰዱ 585 ሺህ 882 ተማሪዎች መካከል 48 ሺህ 929 ተማሪዎች 50 በመቶ በላይ አምጥተዋል።
ባለፈው አመት 5 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች ማለፋቸውን አስታውሰው፤ ዘንድሮ 8 ነጥብ 4 በመቶ ማለፋቸውን ተናግረዋል።
ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ 11 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ 5 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
በተፈጥሮ ሳይንስ ወንድ ከ600 ከፍተኛ ውጤት 591 ሲሆን ከሴት 579 መሆኑን ገልፀዋል።
በማህበራዊ ሳይንስ ከ600 ከፍተኛ በወንድ 562 በሴት 548 መሆኑን ተናግረዋል።
ዘንድሮ 1 ሺህ 249 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ያላሳለፉ ሲሆኑ 50 ትምህርት ቤቶች ደግሞ መቶ በመቶ ያሳለፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ትልቁ ውጤት የመጣው ከአዳሪ ትምህርት ቤቶች አማካይ ውጤቱ 71 በመቶ መሆኑን ጠቁመው፤ ዝቅተኛ የመጣው ደግሞ በማታ ትምህርት ተማሪዎች መሆኑን ተናግረዋል።
2 ሺህ 384 ተማሪዎች ከ500 በላይ ያመጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በዘንድሮ አመት ሬሜዲያል ፕሮግራም እንደሚኖር ገልፀው፤ከባለፈው ዓመት ውጤቱን ከፍ በማድረግ እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት።
በትምህርት ዘመኑ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የትምህርት ስርዓቱን ስብራት ለማከም እየተደረጉ ያሉ የሪፎርም ስራዎችና በፈተና አስተዳደር ስርዓቱ ላይ የተተገበረው ሪፎርም አስተዋፅኦ እንዳለው አንስተዋል።
የፈተናና አስተዳደር ስርዓቱን ከኩረጃና ማጭበርበር ነፃ ለማድረገ የተጀመረው ስራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አንስተው፥ ባለፈው አመት 379 ተማሪዎች ሲያጭበረብሩ መገኘታቸውን አውስተዋል።
ዘንድሮ ይህ ቁጥር ቀንሶ 120 ተማሪ ከሚገባው በላይ ለማግኘት፣ በኩረጃና ተያያዥ ጉዳዮች ሲሳተፉ ተገኝተው ፈተናቸው መሰረዙን ተናግረዋል።
ይህም ተማሪው በስርቆት ሳይሆን ውጤት ጠንክሮ በመስራት የሚገኝ መሆኑን በማመን እየሰራ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል።