ቀጥታ፡

ሙስሊሙ ማህበረሰብ የጣለብንን ሀላፊነት በፍትሀዊነትና በታማኝነት ለመወጣት ዝግጁ ነን

አዲስ አበባ፤መስከረም 4/2018(ኢዜአ)፦ሙስሊሙ ማህበረሰብ የጣለብንን ትልቅ ሀላፊነት በፍትሃዊነትና በታማኝነት ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሱልጣን ሐጂ አማን ኤባ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የ2017 የመጅሊስ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ የእውቅና የማጠቃለያ መርሃግብር አካሂዷል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሱልጣን ሐጂ አማን ኤባ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ የሙስሊሙ ማህበረሰብ በቀጣይ አምስት አመታት ስለመረጠን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነን ብለዋል።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ የጣለባቸውን ትልቅ ሀላፊነት በፍትሃዊነትና በታማኝነት ቀን ከለሌት በማገልገል ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይ አመስት አመታት የትኩረት አቅጣጫ ለይተናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሙስሊሙን መብት ለማስጠበቅ እና አንድነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል፡፡

እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤቱ ለሚያከናውነው ተግባራት ውጤታማነት የሙስሊሙ ማህበረሰብ በጋራ በመሆን እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ የ2017 መጅሊስ ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ጂብሪል ኡስማን በበኩላቸው፥ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

በዚህም በአዲስ አበባ የተከናወነው ምርጫ ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቅ እንደቻለ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ሆነው የተመረጡት ሺሃቡዲን ኑራ በበኩላቸው፥ በቀጣይ የተጣለባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

ሙስሊሙ ማህበረሰብን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የተቋም ግንባታ የልማት ተግባራት ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

ለምርጫው ስኬታማነት አስተዋጽኦ ያደረጉ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሚዲያዎችን ጨምሮ ለተለያዩ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም