ቀጥታ፡

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች 48 ሺህ 929 ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት አልፈዋል-ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፦ በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች 48 ሺህ 929 ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት ማለፋቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ይህም ከአምና ከነበረው 36 ሺህ 409 ተማሪዎች ጋር ሲነፃፀር 12 ሺህ ልዩነት እንዳለው ተገልጿል።

በ2017 የትምህርት ዘመን የተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት በተመለከተ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በ2017 ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 48 ሺህ 929 ተማሪዎች 50 በመቶ በላይ አምጥተዋል።

ባለፈው አመት 5 ነጥብ 4 በመቶ ተማሪዎች ማለፋቸውን አስታውሰው፤ ዘንድሮ 8 ነጥብ 4 በመቶ ማለፋቸውን ተናግረዋል።

ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ 11 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ 5 ነጥብ 2 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

በተፈጥሮ ሳይንስ ወንድ ከ600 ከፍተኛ ውጤት 591 ሲሆን ከሴት 579 መሆኑን ገልፀዋል።

በማህበራዊ ሳይንስ ከ600 ከፍተኛ በወንድ 562 በሴት 548 መሆኑን ተናግረዋል።

ዘንድሮ 1 ሺህ 249 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ያላሳለፉ ሲሆኑ 50 ትምህርት ቤቶች ደግሞ መቶ በመቶ ያሳለፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ትልቁ ውጤት የመጣው ከአዳሪ ትምህርት ቤቶች አማካይ ውጤቱ 71 በመቶ መሆኑን ጠቁመው፤ ዝቅተኛ የመጣው ደግሞ በማታ ትምህርት ተማሪዎች መሆኑን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ፈተና የወሰዱት 585 ሺህ 882 ተማሪዎች ሲሆኑ 308 ሺህ 66ቱ ወንዶች እንዲሁም 277 ሺህ 816 ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም