ቀጥታ፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስኬት ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን በራሳችን አቅም ለመገንባት መሰረት የሚጥል ነው - የመዲናዋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ተጨማሪ ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመገንባት መሰረት የሚጥል መሆኑን የመሰቀል አደባባይ የህዳሴ ግድብ የድጋፍ ትዕይንተ ህዝብ ተሳታፊ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

"ኢትዮጵያ ችላለች፤ በመተባበራችን ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ታላቅ የድጋፍ ትዕይንተ ህዝብ በመስቀል አደባባይ አካሂደዋል።

በትዕይነቱ ላይ ''በኅብረት ችለናል፣ ግድባችን ለተፋሰሱ ሀገራት በረከት እንጂ ጉዳት አይደለም፣ ግድባችን በኢትዮጵያዊነት ኅብር ፀንቶ የመቆም አሸናፊነታችን ኒሻን፣ ግድባችን በወጀብ ውስጥ ሳንናወጥ በቁርጥ ቀን በፅናት እንድንቆም ያደረገን የአንድነታችን ውል መቀነት” የሚሉትን የደስታ መልዕክቶች አስተላልፈዋል።

በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የድጋፍ ትዕይንት ከተሳተፉ የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተስፉ ዋጂ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የእኛነታችን የመቻልና የመተባበር ማሳያ ነው ብለዋል።

ግድቡ በአንድነትና በኅብርና የተመዘገበ ስኬት የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት የማንሰራራት ዘመን መሰረት እንደሆነም ገልጸዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ትዝታ ሽፈራው፤ ጫናን በመቋቋም ለስኬት የበቃው የህዳሴ ግድብ ሌሎች ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን ዕውን ለማድረግ መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ ግዥ የነበራቸውን ተሳትፎም በቀጣይ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በማስቀጠል ለሀገር ዕድገት መሰረት የሚሆን ተሳትፎ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል። 

የትዕይንተ ህዝቡ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ምንዳዬ ገብረሚካኤል፤ ጫናዎችን በመቋቋም ህዳሴ ግድብን በራስ አቅም ማጠናቀቃችን ለሌሎች የልማት ስራዎች ትምህርት ይሆናል ብለዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ኤልሳቤት ተሰማ፤ ህዳሴ ግድብን በጋራ ማሳካት እንደተቻለ ሁሉ በቀጣይ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በትብብርን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

መምህር ከበደ ያደሳ፤ የኢትዮጵያዊያን የኅብር አሻራ ያረፈበት የህዳሴ ግድብ ስኬት በትምህርት ሥርዓት ጭምር በማካተት ለሌሎች የልማት ስራዎች ልምድ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልጽግና በማረጋገጥ መጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር እንዲረከብ ለማስቻል ትብብርና አንድነትን ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም