ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፈጥሮ ሀብትን አልምቶ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማዋል እንደሚቻል ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፈጥሮ ሀብትን አልምቶ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማዋል እንደሚቻል ማሳያ ነው

ደሴ/ደብረብርሃን ፤መስከረም 4/2018(ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተፈጥሮ ሀብትን አልምቶ ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማዋል መቻሉን ያረጋገጠ ነው ሲሉ የደሴና የደብረ ብርሃን ከተሞች ነዋሪዎች ገለፁ።
በከተሞቹ የህዳሴ ግድብ ምርቃትን አስመልክቶ "እመርታና ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።
በደሴ ከተማ በውይይቱ ከተሳተፉት ነዋሪዎች መካከል አቶ ንጉሴ ዓለሙ እንዳሉት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዜጎች አሻራ ያረፈበት ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።
ስኬቱንም በማስቀጠል ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት መረባረብ እንደሚገባ የቤት ስራ የሰጠ ነው ብለዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አውራሪስ ደጀኔ በበኩላቸው ለህዳሴ ግድቡ የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስታውሰው ለምርቃት በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ህዝቡም ይህን ተነሳሽነት በማስቀጠል ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመተግበር መስራት ይገባል ብለዋል።
"የህዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ብርታት፣ ወኔና ጉልበት ሆኖናል" ያሉት አቶ አውራሪስ፤ በቀጣይም ከመንግስት ጎን ተሰልፈን ልማታችንን በማስቀጠል የማንሰራራት ዘመንን ለማሳካት እናሰራለን ብለዋል።
ለግድቡ የገንዘብ፣ የላብና የደም ዋጋ በመክፈል ፣ የውጭና የውስጥ አሉታዊ አስተሳሰብን ያከሸፍንበት ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፋዒዛ ካሳው ናቸው።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለህዳሴ ግድቡ ያሳየውን አንድነት በሌሎችም ልማቶች ሊደገም ይገባል ብለዋል።
ሁሉም መተባበር በመቻሉ የአባይ ወንዝ የተረትና ዘፈን መገለጫ ከመሆን አልፎ ለአገራችን ጥቅም መስጠት ጀምሯል ያሉት ምክትል ከንቲባው ይህም የማንሰራራት ዘመን ብስራት ለመሆን ችሏል ብለዋል።
በተያያዘ ዜና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በከተማዋ በተካሄደው ውይይት እንደገለጹት የግድቡ መጠናቀቅ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን አልምታ በፍትሃዊነት የመጠቀም መብቷን ማረጋገጧም እያደገ የመጣውን ዲጅታላይዜሽን፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ይበልጥ ለማፋጠን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይቱ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል መቶ አለቃ የወንድወሰን ግዛው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ማንሰራራት እውን ለማድረግ መሰረት መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አበራ ሞገስ በበኩላቸው የህዳሴ ግድቡን በርብርብ እንዳሳካነው ሁሉ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ከመንግስት ጎን ቆመን የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።