ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ እና ድልድዮች ይገነባሉ

ወልቂጤ ፤መስከረም 4/2017 (ኢዜአ):- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው በጀት አመት ከ2 ሺህ 291 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የጠጠር መንገድ እና 112 ድልድዮች እንደሚገነቡ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ገለጸ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ኑርዬ (ዶ/ር) እንዳሉት በክልሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ሽፋን በማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማስፋት ይሰራል።

በዚህም  በበጀት ዓመቱ ከ2 ሺህ 291 ኪሎሜትር የሚበልጥ የጠጠር መንገድና 112 ድልድዮች እንደሚገነቡ ገልጸው፤ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ 37 ድልድዮችን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ  ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል። 

እንደ መሐመድ(ዶ/ር) ገለጻ በተያዘው በጀት ዓመት ከሚገነቡት መካከል 10 ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደሚገኙበት ገልጸዋል። 

 ፍትሃዊ የመንገድ  ተደራሽነትን  ማስፋት   የጋራ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል  ያሉት መሐመድ (ዶ/ር)፤ ይህም  ጊዜና  ገንዘብን በመቆጠብ  የኢኮኖሚ እድገትን ያፋጥናል ብለዋል ። 

በመሆኑም በተያዘው በጀት ዓመት ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመቅሰም ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት  እየተሰራ ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ግንባታቸው የቆሙ እና በፕሮጀክት አስተዳደር ችግር ምክንያት የተጓተቱትን  ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።


 

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የረጅም ጊዜ የክልሉ ህዝብ ጥያቄ የነበሩ 3 ሺህ 857 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ እና 33 ድልድዮች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም