ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉበት የ10000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ዛሬ 9:30 ጀምሮ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉበት የ10000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ዛሬ 9:30 ጀምሮ ይደረጋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፦ በጃፓን ቶኪዮ እየተካሄደ የሚገኘው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 የ10000 ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል።
ሰለሞን ባረጋ፣ በሪሁ አረጋዊ እና ዮሚፍ ቀጄልቻ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።
አትሌት ሰለሞን እ.አ.አ በ2023 በሀንጋሪ ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቱ የሚታወስ ነው።
26 ደቂቃ ከ34 ሴኮንድ ከ93 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው።
ሌላኛው ተወዳዳሪ አትሌት በሪሁ አረጋዊ በቡዳፔስት በተደረገው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10000 ሜትር አራተኛ መውጣቱ አይዘነጋም።
26 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ ከ13 ማይክሮ ሴኮንድ የአትሌት በሪሁ የርቀቱ ይግል ምርጥ ሰዓቱ ሆኖ ተመዝግቧል።
አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ 26 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ ከ01 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው። አትሌቱ በቡዳፔስቱ ሻምፒዮና በ5000 ሜትር ተሳትፎ አድርጎ ነበር።
ከፍጻሜው ውድድር ውጪ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ5 በ1 ሺህ 500 ሴቶች ግማሽ ፍጻሜ ውድድር አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ትወዳደራለች።
አትሌት ፍሬወይኒ በምትወዳደርበት ምድብ አንድ ከአንድ እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ይዛ ካጠናቀቀች ለፍጻሜ ታልፋለች።
በተጨማሪም ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከ35 በሚካሄደው የ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ኤርሚያስ ግርማ እና መለሰ ንብረት ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያ በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መክፈቻ በትዕግስት አሰፋ በሴቶች ማራቶን የብር እና በ10000 ሜትር ሴቶች በጉዳፍ ጸጋይ አማካኝነት ማግኘቷ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።