ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የመንፈስ ጥንካሬ ያረጋገጠ ትልቅ ገድል ነው- ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የመንፈስ ጥንካሬ ያረጋገጠ ትልቅ ገድል ነው- ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የመንፈስ ጥንካሬ ያረጋገጠ ትልቅ ገድል ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።
"ኢትዮጵያ ችላለች፣ በመተባበራችን ችለናል" የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ታላቅ የድጋፍ ትዕይንተ ህዝብ በመስቀል አደባባይ ተካሄዷል።
ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያዊያን ላብ እንባና ደም የተገነባውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመደገፍ ከባዱን ዝናብ ተቋቁመው ለተገኙ ተሳታፊዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን አርቀው ያስባሉ፣ ይመራመራሉ፣ ይፈጽማሉ ደግሞም ሰርተው ያሳያሉ፣ ከበረከቱም ያካፍላሉ የሚለውን ትውፊት የሚያሳይ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ፋይዳው ብዙ ነው ብለዋል።
ሕዳሴ ግድብ ሀሳባዊ ሀይሉ ብርቱ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን እንችላለን ማለት ነው፤ በእርግጥም እንችላለን ደግመንም እንችላለን ብለዋል።
ይህም 120 ሚሊዮን ህዝብ ተመልካች ተመጽዋች የሚለውን የመዛበቻ ቅጥያ ስም አሽቀንጥረን ለመጣል ከወሰንን እንችላለን የሚል መልዕክት የያዘ ነው ብለዋል።
እንደ ብርቱ ቋሚና ማገር፣ እንደ ጠንካራ ድርና ማግ ከተቀናጀ ኢላማውንና ግቡን ከለየ ኢትዮጵያዊው ይችላል፣ የሚሳነው ነገር ከቶ አይኖርም ነው የሕዳሴ ግድብ ዋናው መልዕክቱ ብለዋል።
በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትናንት የነበረውን የኢትዮጵያውያን የመንፈስ ጥንካሬ የሚያረጋግጥ ዛሬ ያለንን ጥበብና ብልሃት የሚቃኝ ነገ የሚኖረንን የብርሃን ቀንዲል የሚያሳይ ትልቅ ገድል ነው ብለዋል።
የሚያስቡ አዕምሮዎች ለተግባር የተጉ የጥበብ እጆች ለመጀመርም ሆነ በወጉ ለመጨረስ የተጉ መሪዎች እና ሰራተኞች ሲኖሩ ዕድገት ሀሳብና መልካም ተግባር ተስማሙ ተዋሃዱ ማለት ነው ብለዋል።
የጎበጠን ሀሳብ ለማቅናት አግድም የሄደን የተዛነፈን አፈጻጸም ለማስተካከል የሚተጉ እንዲሁም ስግብግብነትን የሚጸየፉ መሪዎች ሲኖሩ ስራና ሰራተኛ ይስማማሉ ስራ ይሰምራል የስራ ባህልም ይለወጣል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተፋሰሱ ያሉ ጎረቤት ሃገራትን ለመተባበርና አብሮ ለማደግ እድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ በጋራ ለጋራ ልማት መስራት ይገባል ብለዋል።
በማገዶ እንጨት ሸክም የተጎዳ አካላቸውን እንደምን እናቅና እንደምንስ ይቅና ብለን በዓለም አደባባይ ጠይቀናል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ ውድ ኃብት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ለኢትዮጵያ እናቶች የዘመናት እንባ ምላሽ የሰጠ ፕሮጀክት መሆኑንም አንስተዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት ሁሉ ተሳትፎ ላደረጉ አካላት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዋጽኦ ምስጋና የሚገባው ነው ብለዋል።