ቀጥታ፡

የታላቁን የህዳሴ ግድብ ስኬትን በመቀመር የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በትኩረት ይሰራል-ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬደዋ፣መስከረም 4/2018(ኢዜአ)፦የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬትን በመቀመር የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

በአስተዳደሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃን ምክንያት በማድረግ የህዝብን ተሳትፎና አንድነት ለማስቀጠል ያለመ ሳምንታዊ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ ተጀምሯል።

የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕዩን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ለህዝብ እይታ ከፍተውታል።

ከንቲባው በወቅቱ እንደተናገሩት፤ዜጎች በተደመረ መንፈስ በአንድነት ከሰሩ የትኛውንም ሀገራዊ ጉዳዮች በስኬት ማጠናቀቅ እንደሚችሉ የህዳሴው ግድብ ህያው ምስክር ነው።

ይሄን የመደመርና የአንድነት ጉዞ በማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን በመጠበቅ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በላቀ ደረጃ ለመመለስ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

በአዲሱ ዓመትም ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በላቀ ጥራትና ፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ላይ ነዋሪው በህዳሴው ግድብ ያሳየውን ተሳትፎ በተባበረ መንገድ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የድሬደዋ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክርቤት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ዋቅጅራ በበኩላቸው፥ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ህዝባዊ ንቅናቄ ሁነት ህዝቡን ለቀጣይ ልማት ይበልጥ ለማሳተፍ ማለሙን ጠቁመዋል።

የንቅናቄው መድረክ በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ በፓናል ውይይቶች እና በህዝባዊ ሰልፎች እንደሚከበርም ጠቅሰዋል።

ዛሬ የተከፈተውን የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ ከተመለከቱት ነዋሪዎች መካከል አብዱሌ ሮባ እና አቶ ጎዳናው ሚልኬሳ እንዳሉት፤በተባበረ አንድነትና ተሳትፎ የተጠናቀቀው የህዳሴ ግድብ ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ አነሳስቷቸዋል።

በቀጣይም በሚችሉት ሁሉ በድሬዳዋና ሀገራዊ ልማትና ዘላቂ ሰላም ላይ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም