ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከፍጻሜ ለማድረስ የተደረገውን ርብርብ በሌሎች ልማቶች ለመድገም ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከፍጻሜ ለማድረስ የተደረገውን ርብርብ በሌሎች ልማቶች ለመድገም ይሰራል

ጋምቤላ፤መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከፍጻሜ ለማድረስ የተደረገውን ርብርብ በሌሎች ልማቶች ለመድገም ይሰራል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) ገለፁ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት ክልል አቀፍ የድጋፍ ሰልፍ ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እና የፓናል ውይይት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በፓናል ውይይቱ ላይ እንዳሉት፥ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተገኘውን አንፀባራቂ ስኬት በሌሎች የልማት መስኮች ልንደግመው ይገባል ብለዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያውያን በመተባበር መንፈስ ያሳኩት ታሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የማናሳካውና የማንሻገረው ፈተና ያለመኖሩን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።
ይህን ልምድ በመቀመር የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን አክለዋል።
ግድቡ የይቻላልና የአሸናፊነት ስነ-ልቦና በመላው ኢትዮዮጵያዊያን ልብ ውስጥ የተከለ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።
ህዳሴን እውን በማድረግ ያሳየነውን ትብብር በድህነትና በኋላቀርነት ላይ በመድገም ሌላ ታሪክ ለመስራት መትጋት ይኖርብናል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በክልሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ጋትቤል ቦል በበኩላቸው፥ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በይፋ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ህዝብ ያልተቋረጠ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።
ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ ስኬታማነት በገንዘብ፣ በጉልበትና በሃሳብ ሲያደርግ ለነበረው ድጋፍ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ክልሉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያደረገውን አስተዋጽኦ የሚያሳይ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ ለዕይታ ቀርቧል።