ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አብሮ የመስራትና የአንድነት ተምሳሌት ማሳያ ነው

ሮቤ፤መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አብሮ የመስራትና የአንድነት ተምሳሌት ማሳያ መሆኑን የባሌ ሮቤ ነዋሪዎችና አመራር ተናገሩ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ የድጋፍ ሰልፍና ማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሮቤ ከተማ ተካሂዷል።

መርሐ ግብሩን የዞኑ አስተዳደርና የሮቤ ከተማ አስተዳደር በጋራ ማዘጋጀታቸውም ተመላክቷል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ሀይሌ በወቅቱ እንደገለፁት፥ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያንን ያኮራ ተግባር ነው።

ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመተባበር ለትውልድ ጭምር የሚተላለፍ ታሪካዊ ድል ማስመዝገብ እንደሚችሉ በተግባር ያሳዩበት አጋጣሚ መሆኑንም አክለዋል።

የሮቤ ከተማ ከንቲባ ተወካይ አቶ አለማየሁ ቱሉ በበኩላቸው፥ የከተማው ነዋሪ የግድቡን መጠናቀቅ በማስመልከት የተሰማውን ደስታ በተለያየ መልኩ እየገለጸ መሆኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የተደረገው አካላዊ የስፖርት እንቅስቃሴም የዚሁ አካልና በሌሎች ልማት ላይ በአንድነት ለመሳተፍ መነሳሳትን የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል።

በነገው ዕለትም የግድቡን መጠናቀቅ አስመልክቶ የእግር ኳስ ውድድርና የድጋፍ ሰልፍ መርሐ ግብሮች በተከታታይ እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።

በአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሃ ግብሩ ከተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አቶ መሐመድ አህመድ እንደገለጹት፥ የግድቡ በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት በማጠናከር ቀጣይነት ያለው ልማትን ለማሳካት መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።

የኢትዮጵያዊንን የይቻለል መንፈስ በተግባር ያሳየና ለቀጣይ ልማት ወኔን የሚቀሰቅስ ታሪካዊ ድል ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የመርሐግብሩ ተካፋይ አቶ ሙሳ ሀሰን ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም