ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለሚገነቡ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች የምናደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ እናጠናክራለን-የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ የሚገነቡ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች ምጣኔ ሀብታዊ እድገት የሚያፋጥኑ በመሆናቸው ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አስተየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመረቁበት ወቅት ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት ፈሰስ የሚደረግባቸውን የኢትዮጵያን ቀጣይ ሜጋ ፕሮጀክቶች ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

እነዚህም የኒውክሌር ፕላንት በቅርቡ ስራ ማስጀመር፣በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጀመር፣ የመጀመሪያው የጋዝ ፋብሪካ ወደ ስራ ማስገባት ተጠቃሽ ናቸው።

በሚቀጥሉት አምስት ስድስት ዓመታትም ቢያንስ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ገንብቶ ማጠናቀቅ፣የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ማከናወን እና የነዳጅ ማጣሪያ ወደ ስራ ማስገባትም እንደዚሁ።

ኢዜአም ከላይ የተጠቀሱትን ሜጋ ፕሮጀክቶች በተመለከተ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ተዘዋውሮ አነጋግሯል።

የአዲስ አበባ መነዋሪ አለባቸው ገብሬ፥በኢትዮጵያ ለመስራት የታለሙ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።

እንደ ሀገር የሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች ከመጀመር ባለፈ ከፍጻሜ እንደሚርሱ ባለፉት ዓመታት ተገንብተው ለፍጻሜ የበቁ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።

መንግስት ሀገርን የሚቀይሩ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን በማቀዱ ኩራት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ለአብነትም የግብርና ዘርፉ የሚጠይቀውን የግብዓት አቅርቦት በማረጋገጥ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በዚህ ዓመት እንደሚጀመር መገለጹ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብን ከግብ ማድረሳችን የሀገርን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ወደ አንድ ምዕራፍ የሚያሸጋግር አንዱ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ማርቆስ አበበ ናቸው።

አንድን የመሰረተ ልማት ስራ ስናጠናቀቅ ወዲያውኑ ለተጨማሪ የልማት ስራ መሰማራት ይኖርብናልም ብለዋል።

በዚህም መንግስት የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት የቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ያቀደውን እቅድ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ አዲስ መለሰ በበኩሏ፥ መንግስት ይፋ ባደረጋቸው ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መደሰቷን ገልጻለች።

በተለይም ሀገራችን የጋዝ ፋብሪካ ወደ ስራ ማስገባት የምርቶችን አቅርቦት ለማሳደግ የሚያስችል ሀገራዊ ቁልፍ ፕሮጀክት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ፉአድ ታደሰ በበኩሉ፤ በቅርቡ መንግስት ይፋ ያደረጋቸው ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ለዜጎች የስራ ዕድልን በስፋት የሚፈጥሩ ናቸው ብሏል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መታቀዱ እንዳስደሰተው በመግለጽ፤ ይህም ስራ አርሶ አደሩ ማህበረሰብ የማዳበሪያ ምርቶችን በወቅቱ እንዲያገኝ አቅም የሚፈጥር እንደሆነም ተናግሯል።

ዘመኑን የሚዋጅ የአየር ማረፊያ ግንባታ ለማከናወን መታሰቡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ብርሃኑ ወራቦ ናቸው።

መምህር አሰግድ አለማየሁ በበኩሉ፤ ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያን በዓለም ደረጃ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያጠናክሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደ ሀገር የታቀዱ ትልቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም