ኢትዮጵያውያን እንደ ቋሚና ማገር፤እንደ ድርና ማግ ከተቀናጀን የሚሳነን የለም-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን እንደ ቋሚና ማገር፤እንደ ድርና ማግ ከተቀናጀን የሚሳነን የለም-ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤መስከረም 4/2018(ኢዜአ)፡-እንደ ብርቱ ቋሚና ማገር፤እንደ ጠንካራ ድርና ማግ ከተቀናጀን ኢትዮጵያውያን የሚሳነን አለመኖሩን ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ምስክር ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መመረቁን ተከትሎ ''ኢትዮጵያ ችላለች'' በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
በዚሁ ወቅት ፕሬዝዳንት ታዬ ባደረጉት ንግግር፥የሕዳሴው ግድብ ከሁሉ በፊት ሐሳባዊ ኃይሉ ብርቱ መሆኑን አስረድተው፤መልዕክቱም ኢትዮጵያውያን እንችላለን የሚል መሆኑን ገልጸዋል።
አስቸጋሪው ዓለም እናንተ የድህነትና ረሃብ መለያ ናችሁ ሲለን፤ ይህ አመለካከት ሐሰት መሆኑን እና ሠርተን መለወጥ እንደምንችልም ያሳየንበት ነው ብለዋል።
የግድቡ መልዕክት፥እንደ ብርቱ ቋሚና ማገር፤እንደ ጠንካራ ድርና ማግ ከተቀናጀ፤ዒላማውንና ግቡን ከለየ ኢትዮጵያዊ ይችላል፤የሚሳነውም አይኖርም ነው ብለዋል በንግግራቸው።
የሐሳብ ልዕልናውም ኢትዮጵያ ትችላለች መሆኑን አስገንዝበው፥የሥራን ታላቅነትና አሸናፊነት ፍንትው አድርጎ ማሳየቱንም ጠቅሰዋል።
የሚያስቡ አዕምሮዎች፣ለተግባር የተጉ የጥበብ እጆች፣ለመጀመርም ሆነ በወጉ ለመጨረስ የተጉ መሪዎችና ሠራተኞች ሲኖሩ፤ ዕድገት ሐሳብ እና መልካም ተግባር ተዋሃዱ ማለት ነው ሲሉም አብራርተዋል።
የጎበጠን ሐሳብ ለማቅናት የተዛነፈን አፈጻጸም ለማስተካከል የሚተጉ እንዲሁም ስግብግብነትን የሚጸየፉ መሪዎች ሲኖሩ፤ሥራና ሠራተኛ ይስማማል፤ሥራም ይሠምራል፤የሥራ ባህልም ይዳብራል ነው ያሉት።