ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የይቻላል መንፈስን ያጠናከረ ስኬት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የይቻላል መንፈስን ያጠናከረ ስኬት ነው

አሶሳ፤መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የይቻላል መንፈስን ያጠናከረ የስኬት መንገድ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ተናገሩ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የድጋፍ ሰልፍና ማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሂዷል።
የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በወቅቱ እንደገለፁት፣ የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን ህዝብ ያኮራ ትልቅ ሀገራዊ ስኬት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመስራት ስኬት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ያሳዩበት የአይበገሬነት ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በነገው ዕለትም የግድቡን መጠናቀቅ አስመልክቶ የድጋፍ ሰልፍ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም መንሱር በበኩላቸው፥ ህብረተሰቡ የግድቡን መጠናቀቅ አስመልክቶ ደስታውን በአካላዊ የስፖርት እንቅስቃሴ መግለጹን ተናግረዋል።
ይህም የኢትዮጵያዊያን አንድነት በማጠናከር ቀጣይነት ያለው ልማትን ለማሳካት መሰረት እንደሚጥል ጠቁመዋል።
በአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሃግብሩ ከተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አቶ በቀለ ዘሪሁን እና ወይዘሮ አስማረች ደምሴ እንደተናገሩት፥ ግድቡ ኢትዮጵያዊውያንን ያስተሳሰረ እና የይቻላል መንፈስን ያጠናከረ ነው ብለዋል።
በመርሃግብሩ ላይ በህብረት ችለናል፣ግድባችን የማንሰራራት ማሳያ ፣እና ሌሎች መፈክሮች የተሰሙ ሲሆን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።