በታላቁ የህዳሴ ግድብ የታየውን ስኬት በሌሎች የልማት ስራዎች ለመድገም በትጋት ልንሰራ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ የህዳሴ ግድብ የታየውን ስኬት በሌሎች የልማት ስራዎች ለመድገም በትጋት ልንሰራ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤መስከረም 4/2018( ኢዜአ)፦በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የታየውን ስኬት በሌሎች የልማት ስራዎች ለመድገም ጠንክርን ልንሰራ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ አስገነዘቡ።
ይቻላል ብለን ከተነሳን የማይቻል ነገር እንደሌለ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማሳያ ነው ሲል አትሌት ኢብራሂም ጄላን በበኩሉ ገልጿል።
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መመረቅን በማስመልከት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ወጣቶች የተሳተፉበት የሩጫ ውድድር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በወቅቱ እንዳሉት፥ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የታየውን ስኬትና መነሳሳት በሌሎች የልማት ስራዎች ለመድገም በትጋት ልንሰራ ይገባል።
በተለይም ተጀምሮ ፍፃሜውን ያላገኘውን የጋምቤላ ስታዲየም ጨምሮ በሌሎች የልማት ስራዎች ጠንክሮ በመስራት እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር የታለመውን እድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ ጠንክሮ መስራት ይገባል ብለዋል።
በዕለቱ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መመረቅን አስመልክቶ የተካሄደው የሩጫ ውድድር ህዝቡ ደስታውን እንዲገልጽና ለሌሎች ልማቶች እንዲነሳሳ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሯ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኘው ታዋቂው አትሌት ኢብራሂም ጄላን እንዳለው፥ ይቻላል ብለን ከተነሳን የማይቻል ነገር እንደሌለ የህዳሴው ግድብ መሳያ ነው።
በዚህም እንደሚቻል በማቀድ በልማቱም ሆነ በስፖርቱ ዘርፍ ጠንክረን ከሰራን የማናሳካው ነገር አይኖርም ሲል ተናግሯል።
በተለይም የክልሉ ወጣቶች በስፖርቱ ዘርፍ እምቅ አቅም ያላቸው መሆኑን ጠቁመው፥በቀጣይ ለሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉ በርካታ ወጣቶች ከክልሉ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው የሩጫ ውድድር ላይ ርዕሰ መስተዳድሯን ጭምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ወጣቶች ተሳፍዋል።