ቀጥታ፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የብሩህ ተስፋ ቀንዲል፣የማንሰራራት መሰረት ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የብሩህ ተስፋ ቀንዲል፣የማንሰራራት መሰረት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

"ኢትዮጵያ ችላለች፥ በመተባበራችን ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ታላቅ የድጋፍ ትዕይንተ ህዝብ በመስቀል አደባባይ ተካሄዷል።

በድጋፍ ትዕይንተ ህዝቡ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የብሩህ ተስፋ ቀንዲል፣የማንሰራራት መሰረት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡

በአንድ ድምጽ ለተጻፈውና ለማይደበዝዘው፣የወል ትርክታችን የአብሮነት መሰረታችን እንዲሁም በላባችንና በደማችን እውን የሆነው የህዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡

በጉባ ተራራ በቁርጠኝነት እውቀታቸውን ፣ላባቸውን፣ደማቸውንና ህይወታቸውን ለከፈሉ ዜጎች ክብር ይገባቸዋል በማለት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የውስጥና የውጭ ጠላቶች በመተባበር ያሰቡትን ሴራ፣ጥቃትና ስውር ወረራ በጀግንነት በተከፈለ መስዋዕትነት በማለፍ ግድቡን እውን ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በተለይም ባለፉት ሰባት አመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ቁርጠኛ አመራር ግድቡን ከገባበት ቅርቃር በማውጣት እውን ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሂደት የገጠሙንን የተለያዩ ጫናዎች ለመቋቋም የጸጥታ ተቋማት ለከፈሉት ዋጋ ምስጋና አቅርበዋለ፡፡

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ባልተለመደ ሁኔታ ግድቡን አስመልክቶ ከ13 ጊዜ በላይ ስብሰባ መቀመጡን አስታውሰዋል፡፡

ይህ ሙከራ በዲፕሎማቶች በሳል አካሄድ መክሸፉን ጠቁመው፥በዚህ ሂደት ለተሳተፉ ዲፕሎማቶች ምስጋና እቅርበዋል፡፡

የሚዲያ አካላት፣የማህበራዊ ሚዲያ ተዋናዮች፣ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣እንዲሁም እጃችሁ ሳይታጠፍ ድጋፍ ላደረጋችሁ ሁሉ ክብርና ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተሰነዘሩ ጫናዎችን በመተባበር መመከታችን፣ ከተባበርን ምንም ነገር ማሳካት እንደምንችል ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

ምንም አይነት ጫና ከአላማችን ወደ ኋላ ሊመልሰን እንደማይችል የግድቡ መጠናቀቅ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግድቡ እውን መሆን የጂኦ ፖለቲካ አሰላለፉን የቀየረና ኢትዮጵያ መቻሏን ለአለም ያሳየችበት የአይበገሬነት ተምሳሌት የሆነ ዘላለማዊ ሃውልት ነው ብለዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባሳለፍነው ማክሰኞ ጳጉሜን 4/2017 ዓም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መመረቁ ይታወቃል፡፡

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላየም የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የጂቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌህ፣የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼኽ መሐመድ፣የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኬር፣ እና ሌሎች የአፍሪካ እና ካረቢያን ሀገራት መሪዎች መገኝታቸውም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም