የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን የመንፈስ ጥንካሬ የታየበት ታላቅ ገድል ነው -ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን የመንፈስ ጥንካሬ የታየበት ታላቅ ገድል ነው -ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ

አዲስ አበባ፤መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፦ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን የመንፈስ ጥንካሬ የታየበት ታላቅ ገድል ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።
“ኢትዮጵያ ችላለች፥ በመተባበራችን ችለናል” የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የህዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ ታላቅ የድጋፍ ትዕይንተ ህዝብ በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።
በድጋፍ ትዕይንተ ህዝቡ ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ስላሴ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ብዙ ትርጉም ያለዉ መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የመንፈስ ጥንካሬ የታየበት ታላቅ ገድል መሆኑን አንስተዋል።
የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ሀይሉ ብርቱ ተግባሩም ግዙፍ መሆኑን ጠቅሰው፥ የእንችላለን ማሳያ ነው ብለዋል።
120 ሚሊዮን ህዝብ የተመጽዋችነት መገለጫውን አሽቀንጥሮ የጣለበት የብርታት ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድብ የስራ ታላቅነት፣የመሪነት ብቃት፣የህዝብ አንድነት የታየበት መሆኑንም ገልጸዋል::
የዕድገት ግስጋሴ ያለ ኤሌክትሪከ ኃይል የማይታሰብ መሆኑን የተረዳ ትልቅ ስራ ሲሉም ገልጸውታል።
ህዳሴ ከኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ ውድ ኃብት ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ለኢትዮጵያ እናቶች የዘመናት እንባ ምላሽ የሰጠ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።
በህዳሴ ግድብ ሂደት ሁሉ ተሳትፎ ላደረጉ አካላት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዋጽዖ ምስጋና የሚገባው ነው ብለዋል።
በህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ነዋሪዎች የተለያዩ መልዕክቶችን በማንገብ በኅብረ ዜማ ታጅበው ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።