ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ የቴሊግራምና የዋትሳፕ አካውንቶች ላይ ካነጣጠሩ አጭበርባሪዎች መጠንቀቅ አለበት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2018(ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ የቴሊግራምና የዋትሳፕ አካውንት ተጠቃሚዎች ላይ ካነጣጠሩ አጭበርባሪዎች ሊጠነቀቅ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አሳሰበ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ባስተላለፈው የጥንቃቄ መልዕክት እንደገለጸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የቴሌግራምና ዋትሳፕ ተጠቃሚዎች ላይ ያነጣጠረ የማጭበርበርና የአካውንት ነጠቃ እንቅስቃሴዎች እየጨመሩ መጥተዋል።

ከሰሞኑም ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሁኔታ የግለሰቦች የቴሊግራምና ዋትሳፕ አካውንቶች በመረጃ መንታፊዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተነጠቁና ማጭበርበሮች እየተፈጸሙ ስለመሆኑ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሳይበር አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ መስጫ ማዕከል/Ethio-CERRT/ ማረጋገጥ ችሏል።

እነዚህ የአካውንት ነጠቃዎች የሚፈጸሙት ለጥቃት ኢላማ ላደረጉት አካል አጥፊ ተልዕኮ ያላቸውን ሊንኮች በመላክና ሊንኩን እንዲከፍቱ የሚያደርጉ ቴክኒኮችን በመጠቀም መሆኑንም አስታውቋል።

ከነዚህ ቴክኒኮች መካከል በጣም ወሳኝ በሆነ ጉዳይ አስቸኳይ በዙም ወይም በሌሎች የኦንላይን ፕላትፎርሞች ስብሰባ ስለሚኖር በተላከው ሊንክ አማካኝነት እንዲሳተፉ በመደወልና በማግባባት ሲሆን ሊንኩን ከፍተው በሚገቡበት ወቅት አካውንታቸውን ይነጥቃሉ ብሏል።

ከዚህ የአካውንት ነጠቃ በኋላ የተነጠቀውን የቴሊግራም ወይም ዋትሳፕ አካውንት በመጠቀም ወደ ግለሰቡ ወዳጆች ለወሳኝ ጉዳይ ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸዉና እንዲያስገቡላቸዉ በጽሁፍ መልዕክት በመጠየቅ እያጭበረበሩ እንደሚገኙም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገልጿል።

በመሆኑም የቴሌግራምና ዋትሳፕ ተጠቃሚዎች ከማታውቁት አካል አጓጊ የሆኑና አስቸኳይነት ያላቸው ሊንኮች ሲላክልዎት እንዲሁም ሊንኩን እንዲከፍቱ ጥሪ ሲደርስዎት አካውንትዎን ለመጥለፍ ሊሆን ስለሚችል ሊንኮችን ከመክፈት በመቆጠብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልታደርጉ ይገባል ብሏል።

ከዚህ ባሻገር የቴሌግራምና የዋትሳፕ ተጠቃሚዎች ከወዳጅ ዘመድ ወይም የስራ ባልደረባ በእነዚህ አካውንቶች ለሚቀርብ የብድርና የድጋፍ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት በፊት ወደ ጠያቂው ስልክ ደውሎ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም