በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥና ከታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ ተፈቅዷል - የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥና ከታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ ተፈቅዷል - የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2018(ኢዜአ)፦ በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥ እና ከታክስ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥና ከታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ መፈቀዱን አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በዚህም በመጪው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሞተር ጀልባዎችን ከቀረጥና ታክስ ነጻ ወደ ሀገር ማስገባት መፈቀዱን አረጋግጠዋል፡፡
የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮችን በማስፋት ረገድ ከተከናወኑ ስራዎች መካከል የቱሪዝም ልማቱን የማፋጠን ስራ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን አንስተው፤ ኢትዮጵያ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ ሐይቆችን ጨምሮ በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶች እንዳላት ገልጸዋል፡፡
የቱሪስት መዳረሻዎችን በተገቢው መንገድ በማልማት እና በማስተዋወቅ ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽዖ ማበርከት እንዲችሉ ሰፋፊ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪዝምን በመሳብ ረገድ ሊያገለግሉ የሚችሉ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ከ20 በላይ ታላላቅ ሐይቆች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የሀገራችን ሐይቆች የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አመልክተው፤ በመንግስት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በሞተር ኃይል የሚሠሩ የተለያዩ ዓይነት ጀልባዎችን ለአንድ ዓመት ያህል ከቀረጥ እና ታክስ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የገንዘብ ሚኒስቴር መፍቀዱን ተናግረዋል፡፡
ለአንድ ዓመት በሚቆየው ዕድልም ለትራንስፖርት፣ ለግል አገልግሎት፣ ለምርምር እና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች የሚውሉ ጀልባዎችን ማስገባት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች፣ ነጋዴዎች እንዲሁም ሌሎችም ይህን ዕድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡