ቀጥታ፡

በጎንደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን እድገት በማፋጠን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ያደርጓታል

ጎንደር፤ መስከረም 3/2018(ኢዜአ)፡ - በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የኢንቨስትመንትና የልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን እድገት በማፋጠን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ያደርጓታል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ በከተማው በመንግስት፣ በሕብረተሰቡ ተሳትፎና በባለሀብቶች እየተከናወኑ የሚገኙ የኢንቨስትመንት፣ የኮሪደርና ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል፡፡


 

በጉብኝታቸው ማጠቃለያ በሰጡት መግለጫ በአመራሩና በሕብረተሰቡ ቅንጅታዊ ተሳትፎ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራት የከተማውን ገጽታ የሚቀይሩና ሰፊ የስራ ዕድልም የፈጠሩ ናቸው፡፡

የከተማው የኮሪደር ልማት ሰፊ የሕብረተሰብ ተሳትፎ የታየበት፣ ለከተማው ነዋሪዎች ምቹ ጽዱና አረንጓዴ የመኖሪያ አካባቢን በመፍጠር ረገድ የጎላ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የልማት ተነሺዎችን ተጠቃሚ ለማድረግም ከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸው የሼድ ግንባታዎች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ የጎላ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በከተማው የተጀመሩ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራዎች አበረታችና ሞዴል መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህም ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የጎላ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

በግሉ ዘርፍ በሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም በኢንዱስትሪ ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶችም ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት ከተማዋን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ በኩል ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የላቀ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በከተማው የተገነባው ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ሸማቹንና አምራቹን በቀጥታ በማገናኘት የምርት አቅርቦት እንዲጨምርና ገበያን ለማረጋጋት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ሀገር ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ያጠናቀቅነው በራሳችን ገንዘብ እና እውቀት በመሆኑ በልማት ስራዎቻችን የሕብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

በከተማው በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ ሕብረተሰቡ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት፣ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ማበርከቱን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡

በከተማው በፌደራልና በክልሉ መንግስት የበጀት ድጋፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች በጊዜ የለኝም መንፈስ እስከ ምሽት በማከናወን ፕሮጀክቶቹን ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ አመራሩ በየጊዜው ወደ ከተማው በመምጣት የልማት ፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም በቅርብ በመከታተልና በመገምገም እያደረጋቸው ያሉ ድጋፎች ፕሮጀክቶቹን በጥራትና በፍጥነት ለማከናወን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አንስተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል፣ የልማት ተነሺዎችን የሼድ ግንባታ፣ የኮሪደር ልማትና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም