በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የታየው ሕዝባዊ አንድነትና ትብብር በሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የታየው ሕዝባዊ አንድነትና ትብብር በሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

አዲስ አበባ፤መስከረም 3/2018 (ኢዜአ)፦በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የታየው ሕዝባዊ አንድነትና ትብብር በሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የመንግሥት አመራሮችና ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ መመረቃቸው ይታወቃል።
የግድቡን የ14 ዓመት ጉዞ በተለይም የህዝቡን ተሳትፎ የሚያሳይ የፎቶ፣ የስዕል እና በዓባይ ዙሪያ የተፃፉ መፃህፍት አውደ ርዕይ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከፍቷል።
በተመሳሳይ "በህብረት ችለን አሳይተናል" በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ፣ የግድቡ ጂኦስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ፣ የህዝብ አንድነትና ተሳትፎ በተመለከተ የመንግሥት አመራሮችና ምሁራን ሀሳባቸውን አቅርበዋል።
በመርኃ ግብሩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ፥ ግድቡ መቻላችንን ለዓለም ያሳየንበት ነው ብለዋል።
በግንባታው የታየው ሕዝባዊ አንድነት እና ትብብር በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ሕዳሴ ግድብ ትውልዱ በአንድነት ቆሞ የራሱን ደማቅ ታሪክ የፃፈበት መሆኑን ተናግረዋል።
በግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ በሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ሊደገም እንደሚገባ ነው ያነሱት።
የዓባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ጂኦስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጫናን ተቋቁሞ በራስ አቅም ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት ማጠናቀቅ የኢትዮጵያውያንን የመቻል አቅም ያረጋገጠ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ግድቡ በጋራ መቆም ከተቻለ የማይታለፍ ፈተና እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል።
ይህ የጋራ ጉዳይና ሜጋ ፕሮጀክትን በአንድነት የማሳካት ሀገራዊ አቅም ቀጣይነት እንዲኖረው መስራት ከሁሉም የሚጠበቅ የቤት ሥራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ግድቡ ከኃይል ምንጭነት ባሻገር ለዘላቂ የከተሞች እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የተናገሩት የዎርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ካንቲሪ ዳይሬክተር አክሊሉ ፍቅረስላሴ (ዶ/ር) ናቸው።