ቀጥታ፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረጉ  ሜጋ ፕሮጀክቶች የህዝቡን የልማት ጥያቄ የሚመልሱና ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው  -የመዲናዋ ነዋሪዎች 

አዲስ አበባ፤መስከረም 3/2018 (ኢዜአ)፦በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር)  ይፋ የተደረጉ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች የህዝቡን የልማት ጥያቄ የሚመልሱና ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃን በይፋ ባበሰሩበት ወቅት የኢትዮጵያን ቀጣይ ሜጋ ፕሮጀክቶች ይፋ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ በድምሩ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት የሚፈስባቸው የአፍሪካን ልጆች ቀና የሚያደርጉና የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያሳኩ ፕሮጀክቶች እንደሚመረቁና እንደሚገነቡ  መግለጻቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ያደረጓቸው  ሜጋ ፕሮጀክቶች የኒውክሌር ማበልፀጊያ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ፣ የጋዝ ፋብሪካ ምረቃ፣ ከመጀመሪያው የጋዝ ፋብሪካ ከ10 እጥፍ በላይ ከፍ ያለ የጋዝ ማምረቻ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እና የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ናቸው።

በዚሁ ጉዳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ያበሰሯቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በህዝቡ ዘንድ ደስታን መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ሞላ ያለው፤ ፕሮጀክቶቹ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና ጥያቄ የሚፈቱ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 


 

አቶ ገነቱ መርጋ በበኩላቸው ይፋ የተደረጉት ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያፋጥኑ በመሆናቸው ለስኬታቸው ሁለንተናዊ ትብብር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡


 

አቶ አበባው ለሚ ሀገራዊ ፕሮጀክቶቹ ታሪክ ቀያሪ መሆናቸውን በማንሳት፥ ልክ እንደታላቁ ሕዳሴ ግድብ በስኬት ተጠናቀው አገልግሎት እንዲጀምሩ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ጠቅሰዋል።


 

ይፋ የሆኑት ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የወጣቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያሳድጉ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ዓባይነው ሙሉ ናቸው፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ ሜጋ ፕሮጀክቶቹ በርካታ የስራ እድል የሚፈጥሩ መሆናቸውም ለዜጎች ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

ነዋሪዎቹ በአስተያየታቸው ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ሁሉንም የልማት ዘርፍ የዳሰሱ፣ ለህዝቡ አንገብጋቢ የልማት ፍላጎቶች ቅድሚያ የሰጡ ናቸው ብለዋል።


 

በተለይ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱም የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የተሰጠውን ትኩረት ያሳየ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም