በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥ እና ከታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ ተፈቀደ - ኢዜአ አማርኛ
በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥ እና ከታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2018 (ኢዜአ)፦ በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥ እና ከታክስ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥ እና ከታክስ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተፈቅዷል።
በሞተር ኃይል የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥ እና ከታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ መፈቀዱን ለማስታወቅ ከገንዘብ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ የበርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ የዱር አራዊት፣ አእዋፍ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቦታዎች፣ ወዘተ. መገኛ ሀገር መሆኗ ይታወቃል። መንግሥት እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች በተገቢው መንገድ በማልማት እና በማስተዋወቅ ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽዖ ማበርከት እንዲችሉ በማድረግ ረገድ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪዝምን በመሳብ ረገድ ሊያገለግሉ የሚችሉ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ከ20 በላይ ታላላቅ ሐይቆች ያሉ ሲሆን፤ እነዚህ ሐይቆች የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች፣ በእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ የተፈጠሩ ሐይቆች እና ተራራማ ሐይቆች በሚል በሦስት ምድብ ይታወቃሉ።
እነዚህ ሐይቆች በተገቢው መንገድ እንዲለሙ እና የቱሪስት መነሻ በሆኑ ሀገሮች በተገቢው መንገድ እንዲተዋወቁ ቢደረግ ለሀገራችን ተጨማሪ መዳረሻ እና ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ይሆናሉ፡፡ ሀገራችን ቱሪዝምን በመሳብ ረገድ ቀዳሚ ከሆኑ የዓለማችን ሀገሮች አንዷ እንድትሆንም ዕድል ይሰጣሉ፡፡ የአካባቢውን ሕዝብ ኑሮም ያሻሽላሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገቢያችንንም ያሳድጋሉ።
ይህም በመሆኑ እነዚህ የሀገራችን ሐይቆች የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ሲባል የገንዘብ ሚኒስቴር በጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 (እንደተሻሻለ) አንቀጽ 129 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች በሞተር ኃይል የሚሠሩ የተለያዩ ዓይነት ጀልባዎችን ለአንድ ዓመት ያህል ከማናቸውም ቀረጥ እና ታክስ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ የሚያስችል መመሪያ አውጥቷል።
በዚህም መሠረት መመሪያው ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማናቸውም በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ ሰው ወደ ሀገር የሚያስገባቸው፦
1. ፈጣን እና ቅይጥ አገልግሎት የሚሰጡ ለዓሣ ማጥመጃ እና ለአጫጭር ርቀት የመንገደኛ ማጓጓዣ ወዘተ. የሚውሉ አነስተኛ እና መካከለኛ የሞተር ጀልባዎች(outboard motor boats)፤
2. በመካከለኛ ሐይቆች ላይ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ፤ ለቱሪስት እና ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ ፈጣን ጀልባዎች(speedboats);
3. ለቱሪስቶች ጉብኝት አገልግሎት የሚውሉ ግልጽ ወይም በከፊል የተሸፈኑ ጀልባዎች(Tourist excursion boats);
4. ለሰዎች ማጓጓዣ የሚውሉ ጀልባዎች (Ferries);
5. ለጥናት እና ምርምር የሚያገለግሎ ጀልባዎች(Research boats)፤
6. ለግል አገልግሎት የሚውሉ ጀልባዎች (Private motor boats);
7. በጸሐይ ኃይል እና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ጀልባዎች( Eco boats);
8. ጠፍጣፋ እና ባለ ጣሪያ የሞተር ጀልባዎች (pontoon boats);
እና የመሳሰሉት ለሀገራችን ሐይቆች ተስማሚ የሆኑ የሞተር ጀልባዎች ቀረጥ እና ታክስ ሳይከፈልባቸው ወደ ሀገር ሊገቡ ይችላሉ።
ስለዚህ የንግዱ ማኅበረሰብ ይህንን በመረዳት በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሞተር ጀልባዎችን ከቀረጥና ታክስ ነጻ ወደ ሀገር በማስገባት ረገድ በተሰጠው ዕድል እንዲጠቀም እናሳስባለን።
መስከረም 3 ቀን 2018