ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው ትብብርና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለቀጣይ ሀገራዊ የልማት ስኬቶች መሰረት ያኖረ ነው

ወልዲያ/ ገንዳውሃ/  ደብረብርሃን፤ መስከረም 3/ 2018(ኢዜአ)፡- በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው ትብብርና ሕብረ ብሄራዊ አንድነት ለቀጣይ ሀገራዊ የልማት ስኬቶችም መሰረት ያኖረ ነው ሲሉ  በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።

"የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ምልክት" በሚል መሪ ሃሳብ  በወልዲያ፣ ገንዳ ውሃና ደብረ ብርሃን ከተሞች ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሄደዋል። 


 

በወልድያ ከተማ  በተካሄደው መድረክ ከተሳተፉት መካከል  አቶ ኃይሉ አሰፋ እና አቶ ሰማው ተሾመ፤ የሕዳሴ ግድብ ስኬት የሕብረ ብሄራዊ አንድነታችን ማሳያ እና የሁላችንም የኩራት ምንጭ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያዊያን የረጅም አመታት የልማት ውጥን የሆነው ሕዳሴ ግድብ ለስኬት በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይ ሀገራዊ የባሕር በር ጥያቄያችን ምላሽ እንዲያገኝም ጥረትና ትብብራችን ይቀጥላል ብለዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የታየው ትብብርና ሕብረ ብሄራዊ አንድነት ለቀጣይ ሀገራዊ የልማት ስኬቶችም መሰረት ያኖረ መሆኑን ገልጸዋል።

የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ፤ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያስቀመጥነው አሻራ ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር የሁላችንም ቋሚ ቅርስ ነው ብለዋል።


 

በመሆኑም በቀጣይ ሰላምን በማፅናት ልማትና ብልጽግናችንን በማረጋገጥ ለሀገራዊ እድገት መትጋት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

በገንዳ ውሃ ከተማ በተካሄደው መድረክ የተሳተፉት መምሕር ዳኘ አዲስ እና ቆሞስ አባ ወልደ ሰንበት ታምራት፤ የግድቡ ግንባታ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ የታየው ትብብርና ቁርጠኝነት በሌሎች ሀገራዊ የልማት ስራዎችም መቀጠል አለበት ብለዋል።

በግድቡ ግንባታ ያሳየነውን ሕብረትና ያገኘነውን ስኬት ለማስቀጠል እንሰራለን ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አባይነሽ አዛናው ናቸው። 

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊና የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ  ተወካይ አቶ ደረሰ አዱኛ ባስተላለፉት መልዕክት፤  የሕዳሴው ግድብ ስኬት የሁሉም የጋራ ትብብር ውጤት በመሆኑ እንደሚያኮራ ተናግረዋል። 

ሰላምን በማፅናት  ልማትን  አጠናክሮ ለማስቀጠል መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

በደብረብርሃን ከተማ በተካሄደው  ውይይት ላይ የተገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተክለየስ በለጠ እንዳሉት፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያንን ትብብርና አንድነት በዓለም አደባባይ የገለጠ ነው። 

ግድቡ የሀይል አቅርቦትን በማሻሻልና የኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠን ዘላቂ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ በሌሎች ልማቶችም ሕብረተሰቡ ትብብሩን ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የሰሜን ሸዋ ዞን   የሴቶች ክንፍ ሀላፊ ወይዘሮ ንግስት ይጥና በበኩላቸው፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ከግብ ለማድረስ በየደረጃው የሚገኙ ሴቶች በቦንድ ግዥ ያደረጉት አስተዋጽኦ  ከፍተኛ ነው ብለዋልⵆ

በከተሞቹ  በተካሄደው የውይይት መድረኮች ከፍተኛ የመንግስት ስራ  ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም