በሚዛን አማን ከተማ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ወገኖች የማዕድ ማጋራትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በሚዛን አማን ከተማ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ወገኖች የማዕድ ማጋራትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ሚዛን አማን፤መስከረም 3/2018 (ኢዜአ)፦ በሚዛን አማን ከተማ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ወገኖች የማዕድ ማጋራትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
የማዕድ ማጋራቱና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፉ የተደረገው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሸካ፣ ቤንች ሸኮና ምዕራብ ኦሞ ሀገረ ስብከት አማካኝነት ነው።
የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ መልአከ ፀሐይ ብርሃኑ አማረ፤ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስና ለተለያዩ ወገኖች ደግሞ ማዕድ አጋርተናል ብለዋል።
የተቸገሩ ወገኖችን ማገዝና መርዳት ያለው ለሌለው ማካፈል ከጥንት ጀምሮ የመጣ የኢትዮጵያውያን መገለጫ እና መልካም እሴት መሆኑን አንስተው ፤ ለአቅመ ደካሞች የሚደረገው ማዕድ የማጋራትና ድጋፍ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ሀገረ ስብከቱ አድባራትን በማስተባበር የማዕድ ማጋራትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የቤንች ሸኮ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደግፌ ኩድን፤ በቤተክርስቲያኗ የተደረገው የማዕድ ማጋራትና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ስራና የሚመሰገን ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
የድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎችና ወላጆችም በቤተክርስቲያኗ ለተደረገላቸው መልካም ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።