ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የተጎናጸፈችው የዲፕሎማሲ ስኬት ለመላው አፍሪካውያን መነቃቃትን የፈጠረ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 3/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድርድር ሂደት የተጎናጸፈችው የዲፕሎማሲ ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መነቃቃት መፍጠሩን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ምክትል ዳይሬክተሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ በዓለም ላይ ከተገነቡና ከፍተኛ የዲፕሎማሲ አበርክቶ ካላቸው ቁልፍ መሰረተ ልማቶች አንዱ ነው።

የህዳሴ ግድብ በዓለም ላይ ያመጣው ጂኦፖለቲካዊ እና ጂኦስትራቴጂካዊ ተፅዕኖም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያም በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሄደችበት የማይዋዥቅ ዲፕሎማሲያዊ ሂደት በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መነቃቃት መፍጠሩን ተናግረዋል።

በዲፕሎማሲውም መስክ ግንባር ቀደም የሆነው የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ከፍታ ለዓለም አጉልቶ ያሳየ በዘርፉም አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው ይህን ሂደት በሌሎችም ዘርፎች አጠናክሮ ለመቀጠል እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት ያለፈቻቸውን የተንዛዛ የዲፕሎማሲ ሂደት በድል ማጠናቀቋ ለሌሎችም ሀገራት ምሳሌ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አሳሪ የቅኝ ግዛት አካሄዶችን በመሻር በራስ የመወሰን አቅሟን መጠቀም የቻለችበት በቀጣናው እና በአለም አቀፍ ዲፕሎማሲም አዲስ ተሞክሮ የተፃፈበት ስለመሆኑም አመልክተዋል።

የህዳሴ ግድብ የዲፕሎማሲ ሂደቱን አፍሪካ መር የማድረጉ ጥረት ውጤት የታየበትና የኢትዮጵያን ተደማጭነት ያሳደገ ፍትሃዊ እና የሰላ አካሄድ እንደነበርም ገልጸዋል።

የግድቡ መሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠ ጀምሮ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ልዩነት ለማርገብ ሲባል የሶስትዮሽ ድርድር መካሄዱን ያስታወሱት ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲጂታል ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ስለአባት ማናዬ ናቸው።


 

በዚህም ባለፉት 14 ዓመታት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የተሰራው ስራ ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል።

በዲፕሎማሲው መስክ የተመጣበት መንገድ አልጋ በአልጋ አልነበረም ያሉት ዳይሬክተሩ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ይነሱ የነበሩ የስም ማጠልሸቶችን በመቀልበስ እውነታውን ለማስረዳት የተሰራው ስራ ውጤት ተገኝቶበታል ብለዋል።

ግድቡ አዲስ የኢኮኖሚ ፖን አፍሪካኒዝም ምዕራፍን የከፈተና ብሔራዊ የዕድገት ትልሞችን ለማሳካት የሚያስችል የጂኦስትራቴጂ መሰረትን የጣለ ነው ብለዋል።

በአባይ ጉዳይ ያለፍንበት ችግር እና ዲፕሎማሲያዊ ሂደት ብዙ ዕውቀት የተገኘበትና በዓለም አደባባይ ፍትሃዊነትን ለማስፈን የሚደረግ ክርክር ልምድን ያሳደግንበት መሆኑንም አመልክተዋል።

የግድቡ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ የእሳቤ አድማስን ከማስፋት ባሻገር በተናጠል ሳይሆን በጋራ አዲስ ራዕይ ሰንቆ በመንቀሳቀስ ውጤታማ ጂኦፖለቲካዊ አሰራርን ለመተግበር ስንቅ እንደሚሆንም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም