በደሴ ከተማ ለአንድ ሺህ 500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በደሴ ከተማ ለአንድ ሺህ 500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ደሴ ፤ መስከረም 3/2018(ኢዜአ)፡-በደሴ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ ለሚሹ ለአንድ ሺህ 500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
የተበረከተውም 925 ደርዘን ደብተርና 4ሺህ 500 እስክርቢቶ መሆኑንን በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ፍቅር አበበ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በከተማው 69 ሺህ ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ ምዝገባው ቀጥሏል።
እስካሁን ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ ሰኞ መስከረም 5/2018 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራው በይፋ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
ለትምህርት ዘመኑ እስካሁን በተደረገው ጥረት ዘጠኝ ሺህ ደርዘን ደብተር ተሰብስቦ ከ15 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች መከፋፈሉን አንስተዋል።
ዛሬ ደግሞ በውጭ ከሚኖሩ የደሴና አካባቢው ተወላጆች ማሕበር በተገኘ ገንዘብ ለአንድ ሺህ 500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ተገዝቶ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፤ ለተደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።
በማሕበሩ የደሴ አስተባባሪ ማዘንጊያ አበበ በበኩላቸው፤ ማሕበሩ ዛሬ ለአንድ ሺህ 500 ተማሪዎች ያደረገው ድጋፍ 925 ደርዘን ደብተርና 4ሺህ 500 እስክርቢቶ መሆኑን ተናግረዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው የተማሪ ወላጆች ምስጋና አቅርበዋል።