ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የህብረ ብሔራዊ አንድነታችንና የጽናታችን መገለጫ ነው

‎አቦቦ፤ መስከረም 3/2018(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵ የሕዳሴ ግድብ የህብረ ብሔራዊ አንድነታችንና የጽናታችን መገለጫ ነው ሲሉ በጋምቤላ ክልል የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅን አስመልክተው ደስታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ የገለፁ ነዋሪዎች ተናገሩ።

‎"በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ መመረቅን በማስመልከት በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ነዋሪዎች ደስታቸውን በሰላማዊ ሰልፎች ገልጸዋል።

‎ነዋሪዎቹ ደስታቸውን የገለጹት ''የሕዳሴው ግድብ የብልጽግናችን አሻራ ነው፣ 'ግድባችን አንድ ሆነን ብዙ፤ ብዙ ሆነን እንደ አንድ የሆንበት የስብጥራችን ማህተም ነው'' የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮች በማሰማት ነው።

‎ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ የአቦቦ ወረዳ ከነዋሪዎች መካከል አቶ ኪጃክ ኡፒቲ በሰጡት አስተያየት የህብረ ብሔራዊ አንድነታችን መገለጫ የሆነው የሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

‎ሲናፍቁት የነበረው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው የገለጹት ደግሞ ሌላዋ የሰልፉ ታዳሚ ወይዘሮ አቦኖ ኡጆል ናቸው።

‎የግድቡ መጠናቀቅ ቀደም ሲል የነበረውን የፍትህ መጓደል በማስወገድ ዘላቂ ጥቅምን ለሃገራችን እንደሚያመጣም ገልጸዋል።

‎የአቦቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ኡሞድ ኩዎት በወቅቱ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መላ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበትና የመቻልን አቅም ያሳየንበት ፕሮጀክት ነው።

‎የግድቡ ግንባታ በትብብርና በአንድነት ከሰራን የማናሳካው ነገር እንደሌለ ትምህርት ያገኘንበት ነው ሲሉም አክለዋል።

‎የአኝዋ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ኡጁሉ ኡሞድ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የንጋት ጅማሮ ብስራታችን ነው ብለዋል።

‎በህብረትና በአንድነት ተጋምደን ከሰራን ሁሉንም ነገር ማሳካት እንደሚቻል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማሳያ ነው ያሉት ዋና አስተዳደሪው በሌሎች የልማት ስራዎችም ተባብረን በመስራት ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ያገኘናቸው የጂካዎ ወረዳ ነዋሪ አቶ ቢየን ኬት በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁላችንም በአንድነት ሆነን ያሳካነው ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ግድቡ የመላው ኢትዮጵያውያንን አንድነትና ጥንካሬ አጉልቶ ያሳየ ኘሮጀክት መሆኑን ገልፀዋል።

በሕዳሴ ግድቡ የግንባታ ሂደት ላይ አሻራውን ያላሳረፈ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አለመኖሩን ጠቅሰው ግንባታው ተጠናቆ በመመረቁ ትልቅ ኩራት ይሰማናል ብለዋል።

በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የጋራ ትብብር እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ የላቀ ደስታ ፈጥሮብናል ያሉት ደግሞ ሌላዋ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ኛፒኒ ሩት ናቸው ።

በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ያሳየነውን ሕዝባዊ ተሳትፎ በሌሎችም የልማት ስራዎች ላይ በመድገም ሀገራዊ ብልጽግናችንን ልናረጋግጥ ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ገልፀዋል።

በዞኑ የጂካዎ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አንድሪው ቱት በድጋፍ ሰልፉ ወቅት እንዳሉት የህዳሴ ግድቡ መመረቅ ፕሮጀክቶችን ያለማንም ድጋፍ መከወን እንደምንችል በተግባር ያሳየንበት ነው ብለዋል።

የሕዳሴ ግድቡ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶቿን በራሷ አቅም አልምታ የመጠቀም መብቷን ያረጋገጠ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም