ቀጥታ፡

ጽንፈኛው ፋኖ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ በመቀበል በውክልና ጦርነት ሀገር ለማፍረስ እየሰራ ነው

ባህር ዳር፤ መስከረም 3/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛው ፋኖ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ በመቀበል በውክልና ጦርነት ሀገር ለማፍረስ እየሰራ መሆኑን እጁን ለመንግስት የሰጠ የቡድኑ የመረጃና ደህንነት ሃላፊ ያረጋል አያና ገለጸ።

በአማራ ክልል ራሱን “የራስ መንገሻ አቲከም ክፍለ ጦር” ብሎ የሚጠራው ጸንፈኛ ቡድን የመረጃና ደህንነት ሃላፊ የነበረው ያረጋል አያና መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል እጁን ለመንግስት ሰጥቷል።

የጽንፈኛ ቡድኑ መሪዎች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልእኮ ተቀብለው ለማስፈጸም እንደሚሰሩም አጋልጧል።

የጽንፈኛ ቡድኑ ከፍተኛ አመራር የነበረው ያረጋል አያና፤ በተሳሳተ የማህበራዊ ሚዲያ መረጃ ተደናግሮ ጽንፈኛ ቡድንን መቀላቀሉንና ከአባልነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ደረጃ ድረስ መስራቱን ለኢዜአ ተናግሯል።

ጽንፈኛ ቡድኑ በአንደበቱ ለህዝብ እንደሚታገል ቢገልጽም በተግባር ግን የአማራ እናቶች የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ፤ ልጆቻቸውን እንዳያስተምሩ እያደረገ መሆኑንም ተናግሯል።

አርሶ አደሩ ለዘር ያስቀመጠውን እህል እና ለማዳበሪያ የቆጠበውን ገንዘብ ሳይቅር በመንጠቅ ጸረ ህዝብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ነው ያለው።

የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳን በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ወጥተው እንዲሸጡ እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ የሚሰበሰብ ገንዘብን በመንጠቅ ከፍተኛ አረመኔያዊ ተግባር እንደሚፈጽምም አጋልጧል።

ጽንፈኛ ቡድኑ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ህብረት በመፍጠር ሀገር ለማፍረስ የውክልና ጦርነት እያካሄደ መሆኑን ገልጾ፤ ይህም እጅግ አስነዋሪ ተግባር በመሆኑ የመንግስትን የሰላም ጥሪ መቀበሉን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ አስፈጻሚ የሆኑት የቡድኑ አመራሮችም፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በድል በመጠናቀቁ እጅግ ማዘናቸውንም ነው የገለጸው።

በተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎች ተደናግረው ጽንፈኛ ቡድኑን የተቀላቀሉ ወጣቶች የቡድኑን መሰሪ አካሄድ እየተገነዘቡ መሆኑንም ገልጿል።

እነዚህ ወጣቶች ጊዜና ሁኔታዎች ሲፈቅዱላቸው የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁሟል።

ጽንፈኛ ቡድኑ አሁን ላይ እጅግ ተስፋ እየቆረጠ መሆኑን ጠቅሶ፤ ማህበረሰቡ የቡድኑን አፍራሽ ተልዕኮ በመረዳት ከመንግስት ጎን ሆኖ እየታገላቸው መሆኑንም ተናግሯል።

ሁሉም የጽንፈኛ ቡድኑ አባላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ለክልሉ ህዝብ ሰላም ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም