በአረንጓዴ አሻራ የተተከለውን ችግኝ የመንከባከብ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ አሻራ የተተከለውን ችግኝ የመንከባከብ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል

ባሕርዳር፤ መስከረም 3/2018 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከለውን ችግኝ ለውጤት ለማብቃት የመንከባከቡ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት፤ በክረምቱ የተተከለውን ችግኝ የፅድቀት ምጣኔ 85 በመቶ ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ለዚህም ሕብረተሰቡ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በየአካባቢው የተከለውን ችግኝ ለውጤት ለማብቃት የመንከባከብ ተግባር ማጠናከሩን ገልጸዋል።
ሕብረተሰቡ የችግኝን ጠቀሜታ በየጊዜው በውል እየተረዳ መምጣቱን ገልጸው ከ205 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተተከለው ችግኝ ከነሐሴ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የአረምና የመንከባከብ ተግባር በንቃት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ከእንክብካቤው ጎን ለጎንም በጠፋ ችግኝ የመተካት ተግባርም ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከለው ችግኝ የክልሉን የደን ሽፋን በአንድ በመቶ በማሳደግ ወደ 17 ነጥብ 3 በመቶ እንደሚያደርሰው ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ አርሶ አደር አለሙ ወልዴ በሰጡት አስተያየት፤ በክረምት ወቅት በግልና በወል መሬት የተከሉትን ችግኝ በማረም እየተንከባከቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የችግኝን ጥቅም በአግባቡ እየተረዳን በመምጣታችን የእንክብካቤ ተግባሩን እያከናወንን ያለነው በራሳችን ተነሳሽነትና ፍላጎት ነው ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የተከልነው ችግኝ የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስ አግዟል ያሉት ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ አርሶ አደር ተስፋሁን መንጌ ናቸው።
በሰሜን ጎጃም ዞን የአዴት ወረዳ አርሶ አደር ምህረቱ አስማረ፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን የተከሉትን ችግኝ ተንከባክበው እያሳደጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ቀደም ባለው ዓመት የክረምት ወቅት በአማራ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከለው ችግኝ በተደረገለት እንክብካቤ 82 በመቶውን ማፅደቅ ተችሏል።