ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው መክፈቻ ቡዳፔስት ላይ ወርቅ ባገኘችባቸው ርቀቶች የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው መክፈቻ ቡዳፔስት ላይ ወርቅ ባገኘችባቸው ርቀቶች የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2018 (ኢዜአ)፦ በጃፓን ቶኪዮ የሚካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል።
በሻምፒዮናው መክፈቻ ቀን ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ በሚደረገው የሴቶች የ10 ሺህ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ጉዳፍ ጸጋይ፣ ፅጌ ገብረሰላማ፣ ፎይተን ተስፋይ እና እጅጋየሁ ታዬ ይወዳደራሉ።
ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት በሴቶች ማራቶን አትሌት ትዕግስት አሰፋ፣ ሱቱሜ አሰፋ እና ትዕግስት ከተማ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያ በሁለቱም ወድድሮች እ.አ.አ በ2019 በሀንጋሪ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በ10 ሺህ ሜትር ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታ የነበረ ሲሆን ይህም ውጤቷ ጉዳፍ በዛሬው ውድድር ላይ ያለ ማጣሪያ በቀጥታ እንድትሳተፍ አስችሏታል።
በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴቶች ማራቶን በአትሌት አማኔ በሪሶ አማካኝነት ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።
አትሌት አማኔ በህመም ምክንያት በዛሬው ውድድር ላይ ባትሳተፍም ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማራቶኑን ክብር ለማስጠበቅ ይሮጣሉ።