ቀጥታ፡

ከጉባ እስከ ዓለም መድረክ፤ የዓለም አይኖች ያረፉበት የሕዳሴ ግድብ 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም መመረቁ  ይታወቃል። 

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ (ዶ/ር)፣ የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌህ፣ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ (ዶ/ር)፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት፣ የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞትሊ፣ የእስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ሚሶ ድላሚኒ፣ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ፣ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ተገኝተዋል።


 

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዓለምን ዓይን የሳበው የአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በመሆኑ ብቻ አይደለም። ፕሮጀክቱ የአፍሪካን ህልሞች፣ ትብብር እና ቀጣናዊ ትስስር መልህቅ በመሆንም ጭምር ነው።

የምረቃት ስነ ስርዓቱ ከአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓ እና በተቀረው ዓለም በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ዓለም አቀፍ ሽፋን አግኝቷል።

ቢቢሲ በዘገባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ያቆመ የሀገር ኩራት ማሳያ መሆኑን ገልጾ የግድቡ ስኬት የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የዓመታት ጥረትና ድካም፣ በዜጎች የሀብት፣ የጉልበት እና የገንዘብ አስተዋፅኦ የተገኘ ውጤት መሆኑን አመልክቷል።

ግድቡ ለሚሊዮኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን ህይወት እንደሚለውጥ ትልቅ ተስፋ እንደተጣለበትም አመልክቷል። 

ግድቡ የኢትዮጵያውያን ኩራት እና የቀጠናዊ ትብብር ማሳያ መሆኑን አበይት ጭብጡ አድርጎ ዘገባውን የሰራው ዶቼ ቬሌ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ የገንዘብ መዋጮ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝቦች ታላቅ ስኬት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸውን አንስቷል። 

ግድቡ የተፋሰሱ ሀገራት የኢኮኖሚያዊ ውህደት እና ትብብር  መሰረት መሆኑን የጠቀሰው የጀርመኑ መገናኛ ብዙሃን፤ ግድቡ፣ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሌላቸው ኢትዮጵያውን የኢነርጂ አቅርቦትን ከማረጋገጡ  ባሻገር  ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል  በማቅረብ ቀጣናዊ  ጠቀሜታው የጎላ  መሆኑን ገልጿል።
የተርኪዬ ዜና አገልግሎት አናዶሉ የሕዳሴ ግድቡን አስመልክቶ በሰራው ዘገባ የግድቡ ምረቃ ታሪካዊ ድል ሲል በዘገባው ላይ አስፍሯል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ  የነበረውን ኢፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም የቀየረ መሆኑን ጠቅሶ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ትልቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ እውን ማድረግ መቻሏን ጠቅሷል። 

አልጄዚራ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ህልምን እውን ያደረገ ስኬት ነው ሲል በሰራው ዘገባ ያለምንም አይነት የውጭ እርዳታና ድጋፍ ፣በኢትዮጵያውያን የገንዘብ መዋጮና የቦንድ ግዢ መገንባቱ የግድቡን ስኬት የተለየ እንደሚያደርገው ገልጿል። 

በዜጎች ዘንድ ከፍተኛ የባለቤትነት ስሜትና የጋራ ኩራት የፈጠረ ፕሮጀክት መሆኑን ያመለከተው ዘገባው፤ ኢትዮጵያውያን የገጠማቸውን ፈተና አልፈው ያጠናቀቁት ግድብ የሀገራዊ አንድነት ማሳያ እና የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት እንደሆነም አንስቷል። 

ሲኤንን  የሕዳሴው ግድብ  ምረቃ ሀገራዊ ኩራት ምንጭ ሆኗል ያለ ሲሆን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁን የኤሌክትሪክ ሀይል ማመነጫ ግድብ መሆኑንና ለሚሊዮኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ከማረጋገጡ ባለፈ የሀገር ኩራት ምንጭ መሆኑን ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የግድቡ አላማ ወንድም ሀገራትን መጉዳት ሳይሆን ለቀጣናው ብልጽግናን ማምጣት እንደሆነ መግለጻቸውንም በዘገባው ላይ አስፍሯል።  

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅ ኢትዮጵያን የቀጠናው የኃይል ማዕከል ያደርጋታል ያለው ደግሞ አሶሲዬትድ ፕሬስ ነው። 

ኢትዮጵያ የአፍሪካን ትልቁን የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ስትመርቅ፣ ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማሳደግ  ለኢኮኖሚያዊ  እድገት አስተዋፅኦ ከማድረጉ ባሻገር ጎረቤት ሀገራት ኃይል ለመግዛት የሚችሉበትን ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቅሷል።  

ታላቁ የሕዳሴው ግድብ መመረቅ ኢትዮጵያን የቀጣናው የኃይል ማዕከል ያደርጋታል ያለው ደግሞ አሶሲዬትድ ፕሬስ ነው። 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ትልቁን የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ስትመርቅ፣ ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በእጥፍ  በማሳደግ  ለኢኮኖሚያዊ  እድገት አስተዋፅኦ  ከማድረጉ ባሻገር  ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ኃይል ለመግዛት እንደሚያስላቸው ነው በዘገባው ያመለከተው። 

የቻይናው ዢንዋ የሕዳሴው ግድብ ምረቃ የሀገራዊ ስኬት ማሳያ እንደሆነ ጠቅሶ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ትልቁ የውሃ ኃይል ማመንጫ የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በይፋ መርቃለች ሲል ገልጿል። 

በስነ ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያጠናክር፣ የተረጋጋ የኃይል አቅርቦትን እንደሚያረጋግጥና የቀጠናዊ የኃይል ትስስርን እንደሚያሳድግ መግለጻቸውን ዘግቧል። 

በምረቃው ላይ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች መገኘት የፕሮጀክቱን ቀጣናዊ ፋይዳ የሚያሳይ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን ጥቅም ሳይጎዳ በጋራ እድገት ላይ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ማረጋገጣቸውን አውስቷል። 

አጠቃላይ ዘገባዎቹ የሕዳሴ ግድብ በቀጣናው፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የገዘፈ ተጽእኖ የሚያሳይ ነው። 

የሕዳሴ ግድብ ምርቃት ከመገናኛ ብዙሃን ባለፈ በዓለም ደረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦችን ትኩረት ስቧል።

የአሜሪካ የቅድሞ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች እና ታዋቂው የቲክቶክ የይዘት ፈጣሪ ዲላን ፔጅ የሕዳሴ ግድቡ ምርቃትን በአፍሪካ የተሰራ አዲስ ታሪክ ሲል ገልጾታል።

ግድቡ በዓለም ላይ ከሚገኙ 20 ግዙፍ የኤሌትሪክ ማመንጫ ግድቦች አንዱ መሆኑንና ለወደፊት የኢትዮጵያን መጻኢ ጊዜ ብሩህ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግሯል።

ሕዳሴ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ምርት በእጥፍ በመጨመር ሚሊዮኖች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ያስችላል ብሏል።

ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል ለኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ እድገት ትልቅ ሚና እንዳለው የገለጸው ዲላን የጎረቤት ሀገራት ኤሌክትሪክ በሽያጭ እንዲያገኙ ብር የሚከፍት እንደሆነም ጠቅሷል።

ከ17 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የቲክቶክ ተከታይ ባለው የዲላን ፔጅ ገጽ የተላለፈው መልዕክት ይህ ጽሁፍ እስከጠናከረተበት ሰዓት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰው ቪዲዮውን በመውደድ( ላይክ በማድረግ) ድጋፉን ገልጿል። 

በቲክቶክ ገጹ ላይ በጤና እና መዝናኛ ቪዲዮቹ የሚታወቀው የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል የቀድሞ አባል ካጋን ዱንላፕ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት በኢትዮጵያ የኢነርጂ እና የመሰረተ ልማት ዘርፍ ትልቁ የሚባል ስኬት እንደሆነ ገልጿል።

ግንባታው 14 ዓመታት የፈጀው ይህ ግዙፍ የሃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት በራስ አቅም የተገነባና ይህም የብሄራዊ ጥረት ውጤትና የኢነርጂ ሉዓላዊነትን ያረጋገጠ መሆኑን አመልክቷል። 

ይህ የዱንላፕ ቪዲዮ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተከታይ ባለው የቲክቶክ ገጹ ላይ እስከ አሁን ከ165 ነጥብ 6 ሺህ በላይ ተመልካች አይቶታል። 

ኬንያዊቷ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ ብሪላ ናታሻ በቲክቶክ ገጿ ባስላለፈችው የቪዲዮ መልዕክት አፍሪካ በሕዳሴ ግድብ ታሪክ ሰራች ስትል ገልጻለች።

የአፍሪካ የነጻነት ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ ያለ ምንም የውጭ እርዳታ በኢትዮጵያውያን ገንዘብ እና ትልቅ መስዋዕትነት ማሳካቷን ተናግራለች።

ኢትዮጵያ ግድቡን በራሷ እቅም መገንባቷ አፍሪካ መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የማንንም እጅ ሳትጠብቅ መስራት እንደምትችል በግልጽ ለዓለም መልዕክት ያስተላለፈችበት ነው ብላለች።

የግድቡ ምርቃት አፍሪካ በራሷ አቅም የራሷን ጉዳይ ለመፈጸም የወሰደችው ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሳ ምርቃቱ ድንቅ የሚባል ዜና እንደሆነ ተናግራለች።

የቲክቶክ ገጿ ላይ 189 ሺህ 500 ተከታይ ያላት ናታሻ ግድቡን አስመለክቶ ያስተላለፈችው መልዕክት እስከ አሁን ባለው መረጃ 33 ሺህ 800 ሰዎች በመውደድ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።  

ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እና ተጽኦ ፈጣሪ ግለሰቦች ሀሳብ ወጣ ስንል የግድቡ ምርቃት የአፍሪካ የአይበገሬነት እና የጽናት ምልክት፣ ራስን የመቻል እና የቀጣናዊ ዲፕሎማሲ ትብብር መገለጫ ሆኖ የታየበት ነው።  

የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች በምርቃቱ ላይ መገኘት የአፍሪካ ፕሮጀክት የሆነው ሕዳሴ ግድብ ኢኮኖሚን በመቀየር፣ የኢነርጂ ዋስትናና ደህንነት በማረጋገጥ እና ድንበር ተሻጋሪ የዲፕሎማሲ ትስስር መጋመጃ መሆኑም ታይቶበታል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካ የራሷን እጣ ፈንታ በራሷ የመወሰን አቅም እንዳላት የሚያሳይ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በግድቡ ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል። 

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ትልቅ ታሪካዊ አንድምታ አለው ያሉ ሲሆን አፍሪካውያን የራሳቸውን የብልጽግና መሻት በራሳቸው ማካሳት እንደሚችሉም የሚያመላክት መሆኑን አመልክተዋል።

የሕዳሴ ግድብ ከብሄራዊ ፕሮጀክትነት ባለፈ የፓን አፍሪካ አቅምን በተግባር ያሳየና የአፍሪካ መር መሰረተ ልማት ግንባታ መገለጫ ነው ያሉት ሩቶ ግድቡ በቀጣናው ለሰላም እና ብልጽግና ያለንን የጋራ ህልም ማሳካት በእጃችን ያለ ጉዳይ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል። 

በግድቡ ምርቃት ላይ የተገኙት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አህጉራዊ ትብብርና ግንኙነትን የሚያጠናክር የወንድማማችነት ምልክት እንደሆነ ተናግረዋል።  

የላይኛውና የታችኛው ተፋሰሱ ሀገራት መበልጸግ የሚችሉት በጋራ እንደ አንድ ማህበረሰብ በመስራት መሆኑን ገልጸው፤ ውሃና ሌሎች ተፈጥሯዊ ሀብቶች በድንበር የተወሰኑ ሳይሆኑ የወደፊት እጣ ፈንታችንን የሚያስተሳስሩ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።

የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት የሕዳሴ ግድቡ መመረቅ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የኩራት ቀን ነው ያሉ  ሲሆን ግድቡ የኃይል ፍላጎትን ከማሳካት ባለፈ ለልጆቻችን የምንመኘውን የበለጸገ ሀገርና አህጉር ለማስረከብ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን ፕሮጀክት ነው ያሉት ደግሞ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ናቸው። 

ግድቡ የዓለምን ሕዝብ ያስደነቀ የአፍሪካ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሐሙድ አሊ ዩሱፍ ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ ገንብታ ለምረቃ ያበቃችው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሀገሬው አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ብርሃን  ነው ሲሉ ገልጸዋል። 

የዚህ ፕሮጀክት ስኬት ከአኅጉራዊ አጀንዳዎች ጋር የሚጣጣም መሆኑን በመጥቀስ፤ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት ኢትዮጵውያንን እና ቀጣናውን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ በራስ አቅም የገነባችው በመሆኑም፤ የሚደነቅና ለአኅጉራችን መነሳሳትን የሚቸር ተግባር ነው ብለዋል።

5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ሕዳሴ በየቤቱ ብርሃንን በመስጠት፣ ለኢንዱስትሪዎች አለኝታ በመሆንና ከምስራቅ አፍሪካ ባሻገር እድገትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

የሕዳሴ ግድብ ከዲፕሎማሲ አኳያ የአፍሪካ መር ስኬትን በግልጽ የሚያመላክት ነው። ግድቡ በኢትዮጵያውያን የራስ አቅም መገንባቱ አፍሪካ የራሷን የልማት መንገድ በራሷ የመወሰን አቅም እንዳላት የሚያመላክትም ነው።

ግድቡ ኢትዮጵያ እና የተፋሰሱ ሀገራት በትብብርና በውይይት አማራጭ የውሃ ሀብትን ለጋራ ልማት እና እድገት መጠቀም እንደሚቻል በግልጽ ያሳዩበት ነው።

የዓለም አቀፍ መገናኘ ብዙሃንን ከፍተኛ ትኩረት የሳበው የሕዳሴ ግድብ ምርቃት የዜና ዘገባዎች ግድቡ የክፍፍል ሳይሆን የአፍሪካ አንድነት እና ለውጥ ተስፋ መሆኑ ተንጸባርቋል።

ፍሪካ በአጀንዳ 2063 ሁሉን አቀፍ እድገት እና ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ እየተጋች ይገኛል።

ሕዳሴ ግድብ ከዚህ አህጉራዊ ማዕቀፍ አንጻር ትልቅ አህጉራዊ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። 

ግድቡ መብራትን የሚያበራ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን የመልማት አቅም የሚያስመነድግ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።

ዓለም የሕዳሴ ግድብ የራስን መቻል፣ የአይበገሬነት፣ የለውጥ እና መጻኢ ጊዜን ብሩህ የማድረግ ተምሳሌት እንደሆነ በግልጽ መስክሯል። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም